የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች ህዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ ለፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና መርሃ-ግብር ተከናወነ።

አዲስ አበባ ህዳር 20/2004/ዋኢማ/– ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን ልማት ለማገዝ ሲቪል ሰርቪሱ የራሱን ህገ-መንግስታዊና የዜግነት ግዴታውን አውቆ እንዲንቀሳቀስ የሁሉም ኃላፊዎችና አመራር ግዴታ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ጁኔዲን ሳዶ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ጁኔዲን ሳዶ ይህን የገለፁት፤ ስድስተኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች ህዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ ለፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ተቋማት በተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና መርሃ ግብር ላይ ነው።

ህገ-መንግስቱ አዲሲቷን ዴሞክራሲያዊና እኩልነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ የወለደው የህዳሴያችን የማዕዘን ድንጋይ ነው ያሉት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ጁኔዲን ሳዶ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማፈራረስ ዋነኛው መሳሪያ ህገ- መንግስት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በመልካም አስተዳደር፣ በትምህርት፣ በመሰረተ ልማትና በሌሎች ዘርፎች የታዩትን ለውጦች ዳር ለማድረስ የሲቪል ሰርቪሱ ማህበረሰብ ህገ-መንግስቱን መሰረት አድርጎ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረቡት ደግሞ የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ናቸው፡፡

የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት መርሆዎችና የፌዴራል ስርዓቱ እንዲሁም በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት እና የዜጎች ተጠቃሚነት በሚል ርዕስ በቀረቡት ጽሁፎች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ህገ-መንግስቱን በመተግበርና በመጠበቅ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ መናገራቸውን ኢሬቴድ መዘገቡን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ገልጿል።