ለ16ኛው ዓለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስና አባላዘር በሽታዎች በአፍሪካ ጉባዔ የሆቴሎች ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2004/ዋኢማ/-ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ለሚጀመረው 16ኛው ዓለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስና አባላዘር በሽታዎች በአፍሪካ ጉባዔ ለሚሳተፉ እንግዶች ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጥ የሆቴል ዝግጅት መጠናቀቁን  የጉባኤው አዘጋጅ “አይካሳ” አስታወቀ።

የአይካሳ አስተባባሪ ወይዘሮ ዩአዳም ጥላሁን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በጉባዔው ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች የሚያርፉባቸው ሆቴሎች በተገቢው ሁኔታ ዝግጅታቸውን አጠናቀቅ እንግዶቻቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

እንግዶቹ ወደ ሆቴሎቹ ሲመጡ የእንኳን ደህና መጣችሁ ጽሁፍን በየመግቢያ በሮቻቸው ላይ ከመለጠፍ ጀምሮ ስለ ጉባዔው የሚገልፁ የተለያዩ ባነሮችና ብሮሸሮችም በየሆቴሉ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

እንግዶቹ የሚፈልጉትን መረጃ እንዲያገኙ ለማስቻልም ከአዘጋጅ ኮሚቴዎቹ ጋር ሊያገናኙ የሚያስችሉ የስልክ ቁጥሮችን ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶችን መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

እንዲሁም ከቢሸፍቱ ባስ ጋር በመነጋገር ለእንግዶቹ የሚያገለግሉ የትራንስፖርት አገልግሎት መዘጋጀቱንም አስተባባሪዋ ገልፀዋል።

የሆቴል አገልግሎት ያልያዙ እንግዶች ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እንዳይቸገሩ ለማድረግም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅጥር ግቢ ውስጥ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ ባለሙያዎችን መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

አምስት ቀናት የሚካሄደው ይኸው ጉባዔ በኤችአይቪ/ኤድስ፣ በአባላዘር፣ በወባና ቲቢ በሽታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚወያይ ሲሆን፤ በጉባዔው ላይም 10ሺ የሚገመት ተሳታፊ ወደ አዲስ አበባ ሊመጣ እንደሚችል መገለፁ የሚታወስ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።