በኔዘርላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴው ግድብ ከ1ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ አሰባሰቡ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2004/ዋኢማ/- በኔዘርላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ህዳር 16 ቀን 2004 ዓ.ም በሮተርዳም በተከበረው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከቦንድ ሽያጭ ከቶንቦላ ሽያጭና የህዳሴው ግድብ ምስል ካለበት ፒን ሽያጭ በጠቅላላው ከ1 ነጥብ1 ሚሊዮን ብር በላይ አሰባስበዋል፡፡

በብራስልስ ለአውሮፓ ህብረት፣ ለቤልጂየም፣ ኔዘርላንድና ሉግዘንበርግ ሀገራት የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የሆኑት ዶክተር ካሱ ይላላ ሀገራችን በለውጥ ጎዳና እያደረገች ያለችውን የህዳሴ ጉዞ በተፋጠነ መልኩ ዕውን ለማድረግ አስተማማኝ የሆነ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በበዓሉ በኔዘርላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ቀን የፈጠረላቸው ጥሩ ስሜት በጊዜው በነበረው የቦንድ፣ ቶምቦላና ፒን ግዥ ተሳትፏቸውን አሳይተዋል፡፡

በዓሉ የተዘጋጀው በብራስልስ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ ሲሆን በኔዘርላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማስተባበር የተቋቋመው ምክር ቤት አባላትን በዓሉን በማዘጋጀት ሂደት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የኢሬቴድ ዘገባ ያስረዳል።