ጆርጅ ዎከር ቡሽ የኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከልና ለቆጣጠር ቁርጠኛ አመራር ያስፈልጋል

 

አዲስ አበባ ህዳር 24/2004/ዋኢማ/ – የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዎከር ቡሽ የኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቁርጠኛ አመራር እንደሚያስፈልጉ አሳሰቡ።

ጆርጅ ቡሽ ይህን ያሳሰቡት 16ኛ አለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስና የአባላዘር በሽታዎች በአፍሪካ 2011/አይካሳ/ ጉባኤን በተናገሩበት ወቅት ነው።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የመንግስታት ቁርጠኛ አቋም ወሳኝ መሆኑን የገለፁት ጆርጅ ቡሽ የቫይረሱን ስርጭት ወደ ዜሮ ለማምጣት ልክ እንደኢትዮጵያ ቁርጠኛ አመራር ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም የአፍሪካ መሪዎች የኤችአይቪ/ኤድስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እያሳዩ ያለው ቆራጥነትና የሚያደርጉትን ጥረትም ፕሬዚዳንት ቡሽ እንደሚያደንቁ ተናግረዋል።

ቀደም ባሉት አመታት በአፍሪካ የጸረ-ኤችአይቪ መድኃኒትን እንደ ልብ ለማግኘት እድል የነበራቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር ያስታወሱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት፤ የቫይረሱን ስርጭት በመግታትና መድኃኒት በማቅረብ በኩል በተሰራው ከፍተኛ ስራ አሁን የተገኘው ውጤት ማግኘት መቻሉ የሚወደስ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ መንግስት በ2004 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር “የአስቸኳይ ጊዜ የኤችአይቪ/ኤድስ ድጋፍ ለኤድስ ወረርኝሽ” ፈንድ ማድረጉን ጠቁመው፤ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም 39 ቢሊየን ዶላር በጀት መድቦ እንደነበርም ተናግረዋል።

ወደፊትም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዎከር ቡሽ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

ዋኢማ