ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ላለው እድገት የቻይና ባንኮች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2004/ዋኢማ/– ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ላለው እድገት የቻይና ባንኮች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው የቻይናውን ኤግዚም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ዙ ሆንግጂን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለጹት ኤግዚምና ሌሎችም የቻይና ባንኮች ለኢትዮጵያ እድገት ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ ናቸው፡፡

ኤግዚም ባንክ ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል ለኢትዮጵያ የሰጠው ገንዘብ በሙሉ ለታለመለት ዓላማ እንደሚውልና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብም ብድሩ እንደሚከፈል አረጋግጠዋል፡፡

ቻይና ከፍተኛ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ስትሰጥ በቻይና ልማት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችል እንደነበረ መረዳታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ለቻይና መንግሥትና ባንኮች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና በመንግሥት ለመንግሥት፣ በፓርቲ ለፓርቲና በህዝብ ለህዝብ መካከል ያላቸው ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣይም ከቻይና ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የኤግዚም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ዙ ሆንግጂ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለተከታታይ ስምንት ዓመታት ከፍተኛ እድገት በማስመዝገቧና የእድገት ተስፋዋም አስተማማኝ በመሆኑ ባንኩ ግንኙነቱን ያጠናክራል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል 11 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

በቆይታቸው የአዲስ አበባ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክትን ጨምሮ ለሌሎች የልማት ሥራዎች የሚውል የ300 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት የቻይናን መንግሥት በመወከል እንደሚፈራረሙ የኢዜአ ዘገባ ያስረዳል፡፡