በደቡብ በ77 መንገዶች ላይ የግብይት ማዕከላት ሊቋቋም መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፤ ህዳር 26/2004/ዋኢማ/– በደቡብ ክልል በተያዘው ዓመት 77 የመንገድ ላይ የግብይት ማዕከላትን የማቋቋም ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የክልሉ የግብይትና የሕብረት ሥራ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ አያና አበቶ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የግብይት ማዕከላቱ መቋቋም እርሶ አደሮች የእጅ የእደ ጥበብ አምራቾች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች የተሰማሩ ማህበራት ምርቶቻቸውን በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ እንዲያስችላቸው ነው።

የመንገድ ላይ የግብይት ማዕከላቱ የሚቋቋሙት የክልሉን ወረዳዎችና ዞኖች እርስ በእርስና ክልሉን ከጎረቤት ክልሎችና ከአዲስ አበባ በሚያገናኙ ዋና ዋና አውራ መንገዶችን በመጎራበት ነው ብለዋል።

ማዕከላቱ ከአምራቾች በተጨማሪ መደበኛ ሸማቾችና ለተለያዩ ጉዳዮች ከቦታ ቦታ የሚጓጓዙ መንገደኞች እግረ መንገዳቸውን የሚፈልጋቸውን የምግብ፣ የአልባሳትና የተለያዩ ምርቶች ለመግዛት አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው  አመልክተዋል ፡፡

የመንገድ ላይ የግብይት ማዕከላት የበለፀጉ አገራትን ጨምሮ በበርካታ የአውሮፓና የኤሺያ አገራት የተለመዱ መሆናቸውን የገለፁት ኃላፊው፤ ከመደበኛ የግብይት ማዕከላት የሚለዩትም በአነስተኛ ወጪ የሚገነቡ በመሆናቸውና አምራችና ገዥን በቀጥታ በማገናኘታቸው እንደሆነ  ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ማዕከላቱ አምራችና ገዥ ያለምንም ተጨማሪ የግብይት ቅብብሎሽ በቀጥታ ከማገናኘታቸውም በላይ ለሁለቱም ወገኖች ተመጣጣኝ የምርቶች መሸጫ ተመን እንዲኖር በማስቻል ፍትሀዊ የገበያ ሥርዓትን በመፍጠረ በኩል ጠቀሜታ እንዳላቸው  አስረድተዋል፡፡

በደቡብ የግብይትና የሕብረት ሥራ ቢሮ በ2003 የበጀት ዓመት 29 መደበኛ የግብይት ማዕከላትን በማቋቋም ለአገልግሎት ማብቃቱን ኃላፊውን ጠቅሶ የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።