ሕገ መንግሥቱ የብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን መብቶችን በማረጋገጥና ለአገሪቱ ዕድገት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓልጠ/ሚ መለስ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2004/ዋኢማ/ – የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን መብቶችን ያለ ገደብ በማረጋገጥና ለአገሪቱ ዕድገት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከዓመታዊው ”ሕብረ ብሄር” መጽሔት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ጠቅሶ ኢዜአ እንደዘገበው ሕገ-መንግሥቱ ለቡድን መብቶች የሰጠው ትኩረት የዜጎችን መብቶች ለማረጋገጥና የጋራ አገርን ለመገንባት የሚያስችል የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል።

ሕገ መንግሥቱ በአዲሲቱ ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን መብቶች በተሟላ መልኩ እንዲከበሩ ማስቻሉን አመልክተው፣ በዚህም የመበታተን አደጋን አስወግዶ በእኩልነት ለመኖርና ለማደግ አስችሎናል ብለዋል።

የአገሪቱን አንድነት በአዲስ ዴሞክራሲያዊ መሠረት በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ በማቆም ሰላምን በማምጣትና ፈጣን ዕድገት ለማስመዝገብ ሕገ መንግሥቱ ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑንም አቶ መለስ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያዊነት በአንድ ሕዝብና በአንድ ዜጋ ላይ ከውጭ የሚጫን ሸክም ሳይሆን፤እያንዳንዱ ዜጋ ወድዶ፣የኩራቱና የክብሩ ምንጭ መሆኑን አምኖና መርጦ የሚለብሰው ማንነት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ይህም ሕገ-መንግሥቱ ከሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥታት የተለየ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።

”ባለፉት ዓመታት አንዱ ብሄረሰብ ስለ ሌላው ብሄረሰብ ያለው ዕውቀት እየዳበረ መጥቷል። የእያንዳንዱ ብሄረሰብ ሙዚቃ፣ ባህልና አለባበስ የሚያውቅበት በሂደትም የራሱ አድርጎ የሚወስድበት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዚህም የጋራ እሴቶች እየዳበሩ መጥተዋል ብለዋል።

ሕገ-መንግሥቱ ከፖለቲካ መብቶች በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የአካባቢ ጉዳዮችን ጭምር በማካተት ዘመናዊና ተራማጅ ገጽታዎች አላቸው ከሚባሉት ተርታ እንደሚሰለፍም ተናግረዋል።

የአገሪቱ ህዳሴ በብዝሃነት ላይ በተመሰረተው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ተጠቃሚነትና ከትክክለኛ የልማት መሥመር ጋር በማቀናጀት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱንም አስታውቀዋል።

በዴሞክራሲ መርሆዎችና አስተሳሰቦች ዙሪያ የተቀረፀው ሕገ-መንግሥት በአብዛኛው ኢ-ዴሞክራሲያዊ ገጽታዎች የሰፈነበትን ታሪካችን ገጽታ በመቀየር የዴሞክራሲ አስተሳሰብና ባህልን በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚያሰርጹ ተግባራት በስፋት እንደሚከናወኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ገልፀዋል።

”ሕብረ ብሄር” ኅዳር 29 ቀን የሚከበረውን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያዘጋጀው መጽሔት ነው።