3ኛው የከተሞች ሳምንት በደማቅ ስነ ስርአት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2004/ዋኢማ/ – በመቀሌ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 3ኛው የከተሞች ሳምንት ትናንት ማምሻውን በደማቅ ስነ ስርአት ተጠናቀቀ።

በበአሉ መዝጊያ ስነ ስርአት ላይ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፊዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ እንዳሉት በአሉ ለሀገር ገጽታ ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

በ3ኛው የከተሞች ሳምንት የተሳተፉት ከተሞችም ያገኟቸውን ልምዶች ወደ ተግባር መለወጥና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው ጠቁመው ለዚህም ሁሉም አካላት መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የከተማልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ሀይሌ በከተሞች ያለውን የመሬት አስተዳደር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ፍትሃዊነት ያለው እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበአሉ ላይ የተሳተፉ የከተሞች ተወካዮች በበኩላቸው ይህን መሰሉ ውድድር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና እርስ በርስም ጥሩ ተሞክሮና ልምድ እንዳገኙበት ተናግረዋል።

በበአሉ ላይ ከተሞች ባደረጓቸው የተለያዩ ውድድሮች ለአሸናፊ ከተሞች ሽልማት የተበረከተ ሲሆን በመሰረተ ልማት መስፋፋት ባህርዳር፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ በቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በውድድሩ ከተሞች ባላቸው የህዝብ ብዛት በ3 የተከፈሉ ሲሆን በ1ኛው ምድብ በምርጥ ተሞክሮ መቀሌ ከተማ ስትመረጥ ከተማን በማስተዋወቅ የሀረር ከተማ ተመርጣለች።

ውድድሩ ከእስካሁኖቹ በተለየ ሁኔታ በርካታ ከተሞች የተሳተፉበትና ቢሸፍቱ ከባህርዳር፣ ጎንደር ከመቀሌ እና የተለያዩ ከተሞች የእህትማማችነት ግንኙነት መመስረታቸው ለየት እንደሚያደርገውም ተመልክቷል።

4ኛውንና ቀጣዩን ውድድር የአዳማ ከተማ እንድታዘጋጅ መመረጧንም ባልደረባችን መድረክ ልዑል ከመቀሌ ያደረሰችን ዘገባ ያመለክታል።