የአይካሳ 2011 ጉባዔ ዝግጅት የተዋጣለት መሆኑን ተሳታፊ እንግዶች ገለፁ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2004/ዋኢማ/ – 16ኛው ዓለም አቀፍ የኤድስና የአባላዘር በሽታዎች 2011 “አይካሳ” ጉባዔ ዝግጅት የተዋጣለት እንደነበር በጉባዔው ላይ የተሳተፉ እንግዶች ገለፁ።

በጉባዔው ላይ የተሳተፉት አንዳንድ እንግዶች እንደገለፁት፤ ጉባዔው በተገቢው መንገድ የተደራጀና የተዋቀረ በመሆኑ ዝግጅቱና መስተንግዶው የተዋጣለት በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል።

በጉባዔው ላይ ለመሳተፍ ከታንዛኒያ የመጣችው ክላያ ጋሳማጅራ ጉባዔው በጣም ሰፊ፣ በርካታና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ እንግዶችን ያቀፈ ከመሆኑም በላይ የሁሉንም ሰዎች ፍላጎት አርክቶ ማስተናገድ አስቸጋሪ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ተወጥታዋለች በማለት ገልፀዋለች።

ክላያ ከቫይረሱ ጋር የዛሬ 28 ዓመት እንደተወለደች ገልፃ፤ ከጉባዔውም የተለያዩ ተሞክሮዎችን እንዳገኘችና፣ የራሷንም ልምድ ለሌሎች ለማካፈል እድል እንደሰጣት ትናገራለች።

በተለይም ወጣቶች እራሳቸውን ከኤችአይቪ/ኤድስ እንዲጠብቁ ቀድመው በመመርመር እራሳቸውን ማወቅ እንደሚገባቸው ጠቁማ፤ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ወገኖችም እራሳቸውን በመጠበቅ ለሀገር የሚጠቅም ስራዎችን መስራት እንደሚችሉ የራሷን ተሞክሮ በማካፈል ላይ መሆኗን ገልፀዋል።

በሞዛምቢክ ማፑቶ የህፃናት አንድን ድርጅት “ሴፍዘችልድረን” የቅስቀሳና የፕሮግራም ልማት ዳይሬክተር ሌስሌይ ፓትሲያ በበኩሏ፤ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ የመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ገልፃ፤ በድጋሚ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ለመምጣት ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

በጉባዔው ዝግጅት በኩልም ያላትን አስተያየት ስትገልፅ፤ የጉባዔው  ዝግጅት የተዋጣለት እንደነበር ከዝግጅቱ ማየት ይቻላል በማለት ገልፀዋል።

ሌላው ከዛምቢያ የመጣው የብሔራዊ ኤችአይቪ ኤድስ፣ አባላዘርና ቲቢ በሽታዎች ተመራማሪ ሀሮልድ ዊቶላ ስለ ጉባዔው አጠቃላይ ዝግጅት ሲናገር፤ ከመሰብሰቢያ አዳራሽ ዝግጅት ጀምሮ የትራንስፖርት ቅንጅቱና አጠቃላይ ዝግጅቶቹ ሁሉ በጣም ጥሩ እንደነበር ተናግሯል።

እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ እንዳልሆነ ጠቁሞ፤ ሆኖም ኢትዮጵያ ልትታይ የሚገባት ሀገር መሆኗን ተዘዋውሮ ባያቸው ነገሮች ማወቅ መቻሉን ተናግረዋል።

ወደ ሀገሩ በሚሄድበት ወቅትም በጉባዔው ላይ ያገኛቸውን በርካታ ተሞክሮዎችና ስለ ኢትዮጵያዊያን እንግዳ ተቀባይነት ለሀገሩ ህዝብ እንደሚናገር ገልጿል።

ሌላው ፈረንሳዊው ቬሰ ቲዢር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የመጀመሪያው ጊዜ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን ቡና ለመጠጣት በመቻሉ መደሰቱን ገልጿል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን ቡና በመግዛት ወደ ሀገሩ ለመውሰድ ማቀዱን ጠቁሞ፤ አጠቃላይ የጉባዔው ዝግጅት ከጅምሩ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ውጤታማና አስደሳች ነው በማለት ተናግሯል።

ተሳታፊዎቹ አዲስ አበባ ከገቡበት ቀን ጀምሮና እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ገልፀው፤ በአጠቃላይ ዝግጅቱና መስተንግዶ መደሰታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።