ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ቀለበት መንገድ ድልድይ አደባባይ ያለውን መንገድ አሻሽሎ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2004/ዋኢማ/ – የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ቀለበት መንገድ ድልድይ አደባባይ ድረስ ያለውን መንገድ አሻሽሎ ለመገንባት ከቻይና የኮሙኒኬሽን፣ የድልድይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር የ748 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የኮንትራት ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፈቃደ ሃይሌ እና የቻይና የኮሙኒኬሽን፣ የድልድይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ የኢትዮጵያ ቢሮ ስራ አስኪያጅ ዦ ያንግ ሻንግ ናቸው፡፡

ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ኢንጅነር ፈቃደ ሃይሌ እንደገለጹት መንገዱ 4 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር እርዝመትና 40 ሜትር ስፋት አለው፡፡ በተጨማሪም የዋናውን መንገድ 1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመትና የተለያዩ ስፋት ያላቸውን መገናኛ መንገዶች ያካትታል፡፡

በዋናው መንገድ ውስጥም አራት ዋና ዋና የድልድይ ግንባታዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል፡፡ ግንባታው የሚከናወነው ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር ነው ብለዋል፡፡

የመንገዱ መገንባት በነባሩ መንገድ ላይ ማለትም በኦሎምፒያ፣ በወሎ ሰፈርና በቦሌ ሩዋንዳ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት እንደሚያስችልም አመልክተዋል፡፡

መንገዱ ሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነት የምታከናውንበት ዋነኛ በር በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቁመው የመንገዱ ግራና ቀኝ የቢዝነስ አገልግሎት በሚሰጡ ድርጅቶች የተሞላ በመሆኑ ስራቸው እንዳይሰናከል የሚረዳ የግንባታ እቅድና የትራፊክ ማኔጅመንት ፕላን መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ግንባታውን ለማከናወን ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ እንደሚያስፈልግ ከስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም አህጉሪቱ ከምታከብረው የአፍሪካ ሕብረት ምስረታ 50ኛ ዓመት ጋር በማስተሳሰር ዋና ግንባታውን እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር ለግንቦት 2013 ለማጠናቀቅ ተስማምተናል ብለዋል፡፡

የመንገዱ ግንባታ በሚከናወንበት ወቅትም መንገዱ ለትራፊክ ዝግ እንደማይደረግ የተናገሩት ኢንጅነር ፈቃደ ሆኖም በመስመሩ ላይ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች በተቻለ መጠን ሌላ አማራጭ መንገድ ቢጠቀሙ ለስራው መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

የቻይና የኮሙኒኬሽን፣ የድልድይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ የኢትዮጵያ ቢሮ ስራ አስኪያጅ ዦ ያንግ ሻንግ በበኩላቸው ኩባንያው ባለፉት 13 ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ የመንገድ ግንባታ ስራዎች ላይ መሳተፉን ጠቁመው አሁንም ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑም ለኩባንያው ስራ መቃናት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል ሲል የኢዜአን ዘገባ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።