የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ስናከብር ቃል ኪዳናችንን በማደስ መሆኑን ይገባዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2004/ዋኢማ/-ብዝሃነትን በእኩልነት የሚያስተናግደው ህገ-መንግስት የጸደቀበትን ቀን የምናከብረው ሀገሪቱ የተያየዘችውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ቃል ኪዳናችንን በማደስ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ።

ስድስተኛው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀን ዛሬ በመቀሌ ከተማ በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል።

ህገ-መንግስቱን በመፈቃቀድ፣ በመቻቻልና አብሮነትን በማስፈን ለልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበአሉ ላይ ገልፀዋል።

ለዚህም ባለፉት ስምንት አመታት በሀገሪቱ ሰፊ የልማት ብርሃን መፈንጠቁን በማሳያነት አንስተዋል። መላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችም ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመፍጠር የተካሄደው ውስብስብ ትግል በድል እንደተጠናቀቀው ሁሉ የህዳሴው ጉዞም ከዳር እንዲደርስ ርብርቡን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ኤፍ ቢሲ ዘግቧል።

እንዲሁም የብሄር ብሄረሰቦች ቀን መከበር አንድነታችንን የምናጠናክርበት፣ የህዳሴያችንን ጉዞ ለማስቀጠል ቃል የምንገባበት መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃን አስታውቀው፤ ዕለቱ በብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተፈጠረው አንድነት የሚጠናከርበት መሆኑንም ተናግረዋል።

አፈ- ጉባኤው በመቀሌ ከተማ እየተከበረ ባለው 6ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ላይ እንደገለፁት፤ ህገ መንግስቱ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ጠንካራ አንድነት ለመፍጠርና ህዳሴያቸውን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የህገ-መንግስቱን ዋስትና በመጠቀም ተአምር ሊባል የሚችል ለውጥ መመዝገቡን የጠቆሙት አፈ-ጉባኤው የተጀመረውን ልማት በማፋጠንና የህዳሴውን ጉዞ በማስቀጠል ድህነትንና ኋላ ቀርነትን በማስወገድ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት መረባረብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ ተከባብረውና ተቻችለው በመኖር ሀገራዊ የትውልድ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ማድረስ አለባቸው ብለዋል።

በበአሉ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን፤ በኢፊዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በሚል ርዕስ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን፤  የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ረጅም እድሜ ያሰቀጠረ ቢሆንም የህዝቦችን ተጠቀሚነት ያረጋገጠ እንዳልነበረ ተመልክቷል።

አምባሳደር ዲና በጽሁፋቸው ከ1983 ዓ.ም በኋላ የልኡካን ቡድን ወደተለያዩ ሀገራት በመላክ የውጭ ግንኙነቱ እየተጠናከረ የመጣ መሆኑንና በዚህም በሰላምና በልማት በኩል ውጤት እየታየ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በዓሉ በደመቀ ሁኔታ በመቀሌ እየተከበረ ሲሆን፤ ሰባተኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በሚቀጥለው አመት በአማራ ክልል እንደሚከበር መገለፁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።