የሲሚንቶ ዋጋን ለማረጋጋት የተወሰዱ ተግባራት ውጤት እያስገኙ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 2/2004 (ዋልታ) የሲሚንቶ ዋጋን ለማረጋጋት መንግስት በመላው አገሪቱ የወሰዳቸው ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡በቀጣዩ ወራት ወደ ስራ በሚገቡ ሰባት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን ተጨማሪ የሲሚንቶ የማምረት አቅም እንደሚፈጠርም አመልክቷል፡፡ የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በአገሪቱ የሲሚንቶ ፍላጎት ጥያቄን ለመፍታት በተደረገው ጥረት ገበያው እየተረጋጋ ነው፡፡ለገበያው መረጋጋት ዋነኛ ምክንያት መንግስት ለአጭር ጊዜ ባስቀመጠው ከውጭ ሲሚንቶን የማስገባት ተግባር፣ በአገር ውስጥ ያሉት ነባር ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ መደረጉና አዳዲስ ፋብሪካዎች ወደ ስራ እንዲገቡ በመደረጉ ነው ብለዋል፡

፡በዘርፉ ለመሰማራት ፈቃድ ካቀረቡት 37 ፕሮጀክቶች መካከል 15ቱ የማምረት ስራ የጀመሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በግንባታና የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎች ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
በተለይም የሲሚንቶ አቅርቦትና እጥረትን ለማጣጣም በተወሰደው የረጅምና የአጭር ጊዜ መፍትሔ እርምጃ በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ በዓመት 7 ነጥብ 84 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶን ማምረት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ቀጣይ ወራት ወደ ማምረት ደረጃ በሚሸጋገሩ ሰባት ፋብሪካዎች ሊፈጠር የሚችለው ተጨማሪ ሲሚንቶ የማምረት አቅም 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን እንደሚሆንም አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፍጥነት እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ ለማስቀጠል የሚችሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እየተፈጠሩ ሲሆን በቀጣይ እነዚሁ ፋብሪካዎች ሲጠናቀቁ ሌላ የኢኮኖሚ መሰረት እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡

የሲሚንቶ እጥረት የተፈጠረው በመንግስት የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በስፋት መካሔዳቸው፣ የከተሞች መስፋፋትና የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፍላጎት ማደግ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ፖሊሲ በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡