ያለዕድሜ ጋብቻን በመከላከል የሴቶችን ሁለንተናዊ ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባ ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን ገለፁ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2004/ዋኢማ/- በሴት ህፃናቶች ላይ የሚፈፀመውን ያለዕድሜ ጋብቻ እስከመጨረሻው በመከላከል የሴቶችን ሁለንተናዊ ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባ የፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስ ብሔራዊ የሴቶች ጥምረት የቦርድ ሰብሳቢ ክብርት ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን አሳሰቡ።

ቀዳማዊ እመቤት አዜብ መስፍን ትናንት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ ከተማ የከፍተኛ አመራሮች ያለዕድሜ ጋብቻ መከላከልን አስመልክቶ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ያለዕድሜ ጋብቻን በማስቀረት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ የምዕተ አመቱን የልማት ግብ ማሳካት ይቻላል።

ጥምረቱም ያለዕድሜ ጋብቻ በስፋት በሚካሄድባቸው በአማራ፣ ትግራይና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በሶስቱ ክልሎች ባደረገው የተጠናከረ ዘመቻም ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

ጥምረቱ ባለፉት አመታት ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የሚረዱ ከ95ሺ በላይ የማህበረሰብ የውይይት መድረኮችን ያካሄደ ሲሆን፤ በዚህም 3ሺ 304 የሚሆኑ ያለዕድሜ ጋብቻዎች እንዲሰረዙ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

እንዲሁም 288 የፌስቱላ ተጠቂ የሆኑ ሴቶችን በመለየት ህክምና እንዲያገኙ ያስቻለ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥም 214ቱ ህክምናቸውን በተሳካ ሁኔታ በተለያዩ የፌስቱላ ሆስፒታሎች እንዲከታተሉ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ጤናማ ህይወት እንዲኖሩ ማስቻሉን ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን ገልፀዋል።

ከፌስቱላ በሽታ አገግመው የገቢ ምንጭ ለሌላቸው 86 ሴቶች እራሳቸውን እንዲችሉ ለማስቻል የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ የተለያዩ ድጋፎች መደረጉንም አስታውቀዋል።

ጥምረቱ ከዩኤንኤፍፒኤ ጋር በመሆን “ያለዕድሜ ጋብቻ ይቁም!” በሚል በአማራ፣ በትግራይና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እስከ ጎጥ ድረስ በመውረድ የተጠናከረ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ ከሴቶች ማህበራት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ከፍትህ አካላትና ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቆም እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ያለዕድሜ ጋብቻን ለማቆም በሚደረገው ዘመቻ ሁሉም አካላት ከጥምረቱ ጎን እንዲቆሙ ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን ጥሪ አቅርበዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስር በተወካያቸው በአቶ ሀሊል ሙርሳል አማካኝነት እንደተናገሩት፤ በክልሉ ያለውን ያለዕድሜ ጋብቻና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በማስቀረት በኩል ከጥምረቱ ጋር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በክልሉ “አንድም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም” “አንድም ህፃን ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር አብሮ መወለድ የለበትም” በሚል መሪ ቃል ላለፉት 5 ወራት በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች የህብረተሰብ ንቅናቄ በመፍጠር የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የህብረተሰቡን ንቅናቄ በመጠቀም ያለዕድሜ ጋብቻን ለመከላከል ቀደም ሲል ይሰራበት ከነበረው በተሻለ መልኩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ጥምረቱ በክልሉ የሴቶች፣ ወጣቶችንና ህፃናትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ  በማድረግ በኩል የሚበረታታ ስራ እየሰራ መሆኑ ገልፀው፤ ወደፊትም በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የዩኤንኤፍፒ በኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ቤኖይት ካላሳ በበኩላቸው፤ በዓለም ላይ ዕድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ከ25ሺ በላይ ሴት ህፃናት በቀን ለአለዕድሜ ጋብቻ እንደሚዳረጉ ጠቁመው፤ ይህም ችግሩ ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን ያሳያል በማለት ተናግረዋል።

ዩኤንኤፍፒም ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስወገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የውይይት መድረኩም ዩኤንኤፍፒኤ ከጥምረቱ ጋር በቀጣይ በምን አይነት ሁኔታ መስራት እንደሚገባው ማሳያ ነው ብለዋል።

በውይይቱ ወቅት የአማራ፣ ትግራይና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የፀረ-ኤችአይቪ/ ኤድስ ብሄራዊ የሴቶች ጥምረት ቢሮዎች ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፤ በየክልሎች ያለዕድሜያቸው ሊዳሩ የነበሩ ሴቶችና ቀደም ሲል ተድረው በፌስቱላ በሽታ የተጎዱ ሴቶች ተሞክሮዎቻቸውን አቅርበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባዔ ወይዘሮ ሽታዬ ምናሉ፣ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያን ጨምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ አምባሳደሮች፣ የሀይማኖት አባቶችና የክልል ቢሮ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
ዋኢማ
አዓ