ኢትዮጵያና ሕንድ በግብርና ምርምር ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2004/ዋኢማ/ – ኢትዮጵያና ሕንድ በግብርና ምርምር ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ትናንት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና የሕንድ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሥራ ኃላፊዎች ፈርመዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በሁለቱ አገራት የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መካከል የተደረገው ስምምነት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የሚያጠናክር ነው።

በተለይ ሁለቱ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች በጋራ የሚያከናውኗቸው የግብርና ምርምሮች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት አገር በመሆኗ በርካታ የሕንድ ባለሀብቶች በግብርና ዘርፍ ተሰማርተው እንደሚገኙም አብራርተዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በተጨማሪ በርካታ የእንስሳት ሀብት ያላት አገር መሆኗንም አስረድተዋል።

ይህ ደግሞ የሕንድ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በስጋና በወተት ተዋጽኦ ዙሪያ ምርምር ለማድረግ መልካም አጋጣሚ እንደሆነም አቶ ወንድይራድ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሚስተር ባግዋንት ቢሽኖይ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የሕንድ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያከናውናቸው የግብርና ምርምሮች ዙሪያ በተዘጋጀው የሥራ ዕቅድ ላይ ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንዲሁም የሕንድ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የረጅም ጊዜ የግብርና ምርምር ልምድ ያለው ተቋም በመሆኑ ለኢትዮጵያ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ፍላጎት እንዳለውም ኢዜአ ዘግቧል።