ኢትዮጵያ በ2012 በለንደን ለሚካሄደው ኦሎምፒክ ሰፊ ዝግጅት እያከናወነች መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2004/ዋኢማ/ – ከስምንት ወር በኋላ በእንግሊዝ ለንደን ለሚካሄደው 30ኛው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የተሻለና የተሳካ ውጤት ለማግኘት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ።

ትላንት በሂልተን ሆቴል ለንደን 2012 ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ዝግጅትና ተሳትፎን አስመልክቶ በተዘጋጀ  መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንትና የለንደን ኦሎምፒክ አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም  እንደተናገሩት፤ በለንደን 2012 ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን ወክሎ የሚካፈለው የልዑካን ብድን ለውጤት እንዲበቃ ኮሚቴው ሰፊ ዕቅድ በማውጣት የሚጠበቅበትን እያከናወነ ይገኛል። 

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሀምሌ 27 ተጀምሮ ነሀሴ 12 ቀን 2012 የሚጠናቀቀው 30ኛው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ለመሳተፍ በ29ኛው ማለትም በ2008 የቤጂንግ ኦሎንፒክ ውጤት መነሻ በማድረግና በዛን ወቅት የነበሩትን ደካማና ጠንካራ ጎኖች በመፈተሽ ወደፊት ለሚጠበቀው የኦሎምፒክ ውድድር ዝግጅት መጀመሩን  መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ያሉትንም ነባራዊ እውነታዎች በማስቀመጥ የዝግጅት ስራውን ከአንድ ዓመት በፊት መጀመሩን የተናገሩት አቶ ብርሃነ፤ ዝግጅቱ ጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዝግጅቱ መሳካትም ዕቅዶችን በማውጣትና በማስፈፀም በኩል የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን፣ የብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች፣ የዝግጅቱ ዓብይ ኮሚቴና ሶስት ንዑሳን ኮሚቴ ያለው ማለትም የስልጠናና ዝግጅት፣ የስፖንሰርሺፕና የኮሙኒኬሽን ንዑሳን ኮሚቴዎች የሚሳተፉበትን መዋቅር በመፍጠር እቅዱን የሚያሳኩ አበረታች ጅምር ስራዎች በመስራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኦሎምፒክ ውድድሩን በማንኛውም መልኩ ለማገዝ የሚፈልጉ ዜጎችም የኦሎምፒክ ኮሚቴው ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አቶ ብርሃነ ገልፀዋል።
 
እስካሁን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በስልጠና ረገድ ለስምንት ወጣትና ተተኪ አትሌቶች ሙሉ ወጪያቸውን የሸፈነ በስኮላርሽፕ የተሸፈነ ሲሆን፤ ለ60 አሰልጣኞችና የህክምና ባለሙያዎች የስፖርት ህክምና ኮርስና ለ120 ባለሙያዎች የአትሌቲክስ፣ የውሀ ዋና፣ የዎርልድ ቴኳንዶና የቦክስ ስፖርቶች ኮርስ ስልጠና ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ብርሃነ ገለፃ ካሁን ቀደም በ29ኛው የቤጂንግ ኦሎምፒክ የተገኘውን ሰባት የሜዳሊያዎች ብዛት በለንደን በሚካሄደው ኦሎምፒክ በ40 በመቶ ከፍ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማግኘት መታቀዱን ገልፀዋል።

እንዲሁም የለንደን ኦሎምፒክ ሀገሪቱ አንጸባራቂ ድል የምታስመዘግብበት ብቻ ሳይሆን ከዚህ ባለፈ መልኩ ኢትዮጵያን ለዓለም ለማስተዋወቅ የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በኦሎምፒኩ ለሚካፈለው ቡድንም 30 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን ገልፀው፤ ለዚህ ስኬትም መላው ህብረተሰብ፣ መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የግል ባለሀብቶች ለዚሁ ዓላማ ተብሎ በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ እንዲሳተፉና አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስፖርት ማዕከላትና ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በሀገሪቱ ለማስፋፋት ከአዲስ አበባ መስተዳድር በተገኘ ግምቱ 43 ሚሊየን ብር የሚገመት 120 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሁለገብ የኦሎምፒክ አካዳሚ ለመገንባት የዲዛይን ስራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነርና የአቢይ ኮሚቴው የበላይ ጠባቂ አቶ አብዲሳ ያደታ በበኩላቸው፤ በለንደን ኦሎምፒክ ጥሩ ውጤት ለማምጣት የሚመለከታቸው አካላትና ህብረተሰቡ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ለዝግጅቱ መሳካት የኦሎምፒክ ኮሚቴው ያዘጋጀው የእቅድና መመሪያ ሰነድም ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ስምንት ወራት ብቻ የቀረው የኦሎምፒኩ ውድድር ኢትዮጵያ በአራት የስፖርት ዓይነቶች ማለትም በአትለቲክስ፣ ቦክስ፣ በውኃ ዋናና በወርልድ ቴኳንዶ እንደምትካፈል መገለፁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
ዋኢማ