ተያዘው የበጀት ዓመት 20 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የ79 የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይከናወናሉ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4 /2004/ዋኢማ/-  በተያዘው የበጀት ዓመት 20 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ 79 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።

በባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንዳስታወቁት የ2004 የበጀት ዓመት የአራተኛው ዙር የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ሁለተኛ ዓመት ማስፈፀሚያ ወቅት ነው።

አንደኛውና ሁለተኛው ዙር የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሞች ትኩረት የነበረው የነባር መንገዶችን ደረጃ ማሻሻልና በማሳደግ ላይ እንደነበር አስታውሰው፣ አራተኛው ዙር የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም የትኩረት አቅጣጫ ደግሞ ቀደም ሲል የመንገድ አውታር ያልተዳረሰባቸውን የአገሪቱን ክፍሎች የመንገድ ተጠቃሚ ያደርጋል።

ሦስተኛውና በተለይም በአራተኛው ዙር የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም የሁለተኛ ዓመት ማስፈፀሚያ በሆነው የ2004 የበጀት ዓመትም በርካታ መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተነድፈው ወደ ትግበራ በመሸጋገር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

አቶ ሳምሶን እንደገለጹት በፕሮግራሙ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ5ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው 79 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ይከናወናሉ።

ከፕሮጀክቶቹ መካከልም በ2003 በጀት ዓመት ግንባታቸው የተከናወኑ 665 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍኑት ስምንት ፕሮጀክቶች የማጠናቀቂያ፣ የመያዣና የማስተካከያ ስራ እንደሚከናወንላቸው ተናግረዋል።

ከነዚህም መካከል የሻሁራ-ገላጐ እና የማኛ-መቻራ የሚዘልቀው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

እንዲሁም ግንባታቸው ካለፉት ዓመታት የቀጠሉ ከ2ሺ 477 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው የ30 መንገዶች ግንባታ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።
 
ከነዚህም ዱርቤቴ-ሻሁራ፣ ማኛ-መቻራ፣ ሐውሰዋ-አባአላ-ኢረብቲ፣ ሠመራ-ዲዲግሣላ-ያሎ፣ እንዴቶ-ጋሰራ፣ አሶሳ-ኩርሙክ፣ ሳንጃ-ቀራቀር እና የአርባምንጭ-በልታ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።

በበጀት ዓመቱ የአዳዲስ መንገዶችን ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ገልጸው፣ በተያዘው የበጀት ዓመትም የዝግጅትና የግንባታ ሥራዎች የሚያካሂዱ 15 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከፕሮጀክቶቹ መካከልም ሣውላ-ቃቆ፣ ዲማ-ፍየልውሃ፣ አብአዲ-ሃውላሄን-ሰንቃጣ፣ ደባርቅ-ቡሃይት-ድልይብዛ፣ መሃልሜዳ-አሶሳ፣ ሴሩ-ሸነን ወንዝና ያቤሎ-ሜታገፈርሳ የመሳሰሉት ፕሮጀክቶች ግንባታውን ለመጀመር የሚያስችሉ ሥራዎች ያከናውናሉ።

ፕሮጀክቶቹ ቀደም ሲል ምንም አይነት የመንገድ አውታር ባልነበረባቸው አካባቢዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በቀጣዩ ዓመት ግንባታቸውን ለሚከናወኑ 1ሺህ 218 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 25 አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች የቅድመ ክፍያና የዝግጅት ሥራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።

በልታ-ሳውላ፣ ሞጣ-ጀራ-ገዶ፣ ሳላይሽ-ኦሞ-ማጂ፣ ደብረብርሃን-አንኮበርና ያሎ-ነሂሌ ከፕሮጀክቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ የሚውለው ወጪ በመንግሥት እንደሚሸፈን ዳይሬክተሩን በመጥቀስ የዘገበው ኢዜአ ነው።