ጃፓን በሁለት ክልሎች የንጹህ ውኃ መጠጥ አቅርቦትን የሚያሻሽል ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2004/ዋኢማ/ – የጃፓን መንግሥት በአፋርና በአማራ ክልሎች የንጹህ ውኃ መጠጥ አቅርቦትን የሚያሻሽል የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ትናንት ተፈራረመ።

በጃፓን ኤምባሲ በተካሄደው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት የጃፓን መንግሥት በክልሎቹ ንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሻሻል ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምቷል።

በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በአፋር ክልል ዞን አምስት የደዌና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የአለፋ ወረዳዎች ንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት የማሻሻል ሥራ እንደሚሰራበት ተገልጿል።

ስምምነቱን በጃፓን በኩል የፈረሙት በኢትዮጵያ የአገሪቷ ኤምባሲ ዋና ጉዳይ አስፈጻሚ ሚስተር ዮሺያኮ ኢቶ፣ በአፋር ክልል በኩል ደግሞ የአፋር ማኅበረሰብ ዘላቂ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ መሐመድ ሲፈርሙ የአፍሮ ኢትዮጵያ የተቀናጀ ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺመታ እዘዘው ደግሞ በአማራ ክልል በኩል ስምምነቱን ፈርመዋል።

ሚስተር ኢቶ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት የጃፓን ሕዝብና መንግሥት ድጋፍ እንደማይለያት አረጋግጠዋል።

ድጋፉ በንጹህ ውኃ መጠጥ አቅርቦት ረገድ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ለማሳካት አገሪቷ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

አቶ አህመድ በበኩላቸው ድጋፉ በክልሉ ትምህርት ቤቶች ንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሽፋን በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተው፣በደዌ ወረዳ ለሚገኙ 18 ሺህ የአፋር ማኅበረሰብ አባላት የንጹህ ውኃ አቅርቦት በማሻሻልና በተለይ ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን ለመከታተል ያስችላቸዋል ብለዋል።

አቶ ሺመታ በበኩላቸው መንግሥት የሚያደርገውን የልማት ጥረት በኅብረተሰቡ የተቀናጀ ጥረት መደገፍ ከተቻለ ዘላቂ ልማትን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ከዚህ አንጻር የጃፓን መንግሥት ያደረገው ድጋፍ ኅብረተሰቡ የመንግሥትን የልማት ጥረት ለመደገፍ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያጎለብት ነው።

ከጃፓን መንግሥት በተገኘው የልማት ትብብርም በአለፋ ወረዳ 15 ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶችን በመቆፈር 13 የሚጠጋ ሕዝብ ተጠቃሚ እንሚያደረግ ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።