ቢሮው የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው

ሀዋሣ፤ ታህሳስ 4/2004/ዋኢማ/- የደቡብ ክልል የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የክልሉ የሴቶች የሕፃናትና ወጣቶች ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ነስረዲን መሐመድ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ ወጣቶቹን የመደገፍ ሥራዎቹ በመከናወን ላይ የሚገኙት በክልሉ ባሉ 14 ዞኖችና 3 ልዩ ወረዳዎች ውስጥ ነው።

ቢሮው የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ ባደረገው ጥረት ከ69 ሺ በላይ ወጣቶችን በመመልመልና በገጠር ከተዘረጋው የብድር ማዕቀፍ ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን የሥራ ሂደት አስተባባሪው ተናግረዋል።

ወጣቶቹ በአሁኑ ወቅት በተመቻቹላቸው የሙያ ክህሎት ሥልጠናዎች፣ የብድር፣ ማምረቻ ቦታዎችና የገበያ አቅርቦቶች በመጠቀም ራሳቸውን ወደ መቻል መሸጋገራቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም 19 ሺ ለሚጠጉ የገጠር ሥራ-እጥ ወጣቶች በማንም ይዞታ ሥር ያልዋሉና ሊታረሱ የሚችሉ የእርሻ መሬቶችን በማከፋፈል በግብርና ምርት ሥራ እንዲሠማሩ መደረጉን አስረድተዋል።

እንዲሁም ቢሮው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር በመቀራረብና ሁኔታዎችን በማመቻቸት ለህብረተሰቡ ተከታታይነት ያለው ነጻ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ወጣቶች እየሰጡ በሚገኘው የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል፣ በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋጾ በማበርከት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ወጣቶች ዘንድ የበጎ ፍቃደኝነት ባህል እየተለመደ በመምጣቱ  ወጣቶቹ ማህበራዊና ልማታዊ ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም የመፍታት ባህል እያዳበሩ መምጣታቸውን መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።