የአፍርካ ህብረት ሳይንስና ቴክኖሎጂን መሰረት አድርገው የሚሰሩ 5 የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ማቋቋሙን ገለፀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2004/ዋኢማ/ – የአፍርካ ህብረት ሳይንስና ቴክኖሎጂን መሰረት አድርገው የሚሰሩ 5 የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች በ5 የአፍሪካ ሀገራት ማቋቋሙን ይፋ አደረገ፡፡

ዩኒቨርስቲዎቹ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂን፣ እርሻን፣ ጤናን፣ የኃይል አጠቃቀምን እንዲሁም ማህበራዊ ሳይንስን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ናቸው፡፡

ዩኒቨርስቲዎቹ የተከፈቱባቸው ሀገራት ከሰሜን አፍሪካ አልጀሪያ፣ ከምስራቅ አፍሪካ ኬንያ፣ ከምዕራብ አፍሪካ ናይጀሪያ፣ ከመካከለኛው አፍሪካ ደግሞ ካሜሩን ናቸው፡፡

በደቡባዊ አፍሪካ ክፍል የሚከፈተው ዩኒቨርስቲም በየትኛው ሀገር እንደሚሆን ወደፊት ይፋ ይሆናል ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዣን ፒንግ ዩኒቨርስቲዎቹ በአህጉሪቱ መከፈታቸው አፍሪካን በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ለማገናኘት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎቹ በዓመት 500 አፍሪካውያንን በ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ እንደሚያስተምሩም ይጠበቃል፡፡

በሌላ ዜና በአፍሪካ በሳይንስ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሴቶች የሚሰጠው የ2011 የክዋሚ ኑኩርማህ የሳይንስ ሽልማትም ለ7 አፍሪካዊ ሴቶች ተሰጥቷል፡፡

ተሸላሚዎቹ ከግብጽ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከካሜሮን፣ ከኮትዲቭዋር እንዲሁም ከናይጀሪያ የመጡ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው ሰርተፍኬት እና የ20 ሺ ዶላር ሽልማት እንደተበረከተለቸው የኢሬቴድ ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።