አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2004/ዋኢማ/ – የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በትናንትናው ዕለት ባካሄደው የአባልነት ወንበር ጨረታ 92 የተለያዩ ወንበሮች ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣታቸውን አስታወቀ፡፡
የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር እሌኒ ገብረመድህን በሰጡት መግለጫ ወንበሮቹ ዋጋውን ያወጡት በነጭና ቀይ ቦሎቄ እንዲሁም በሰሊጥ ምርት በውስን አባልነት በተሳተፉና ለአዲስ ፈላጊዎች ክፍት በነበረ ጨረታ ነው፡፡
በዕለቱ ውስን አባል ለነበሩ አቅራቢዎች 50፣ ለላኪዎች 25ና ለሌሎች ፈላጊዎች 17 በአጠቃላይ 92 አዲስ ወንበሮች ቀርበው 123 ሚሊዮን 370 ሺ 709 ብር አውጥተዋል።
በትናንትናው ዕለት ለጨረታ የቀረበው የአባልነት ወንበር አማካይ ዋጋ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር መድረሱንና ይህም ካለፈው ጋር ሲነጻጸር በ27 እጥፍ ማደጉን ዶክተር እሌኒ አብራርተዋል።
የአባልነት ወንበሩ ቋሚ መሆኑንና ወደፊት ሊሸጥ፣ ሊለወጥና በውርስ ሊተላለፍ የሚችል የግብይት መብት እንዳለም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስረድተዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜም ዋጋውና ጠቀሜታው እያደገ የሚሄድና ውስን አባላት እንዳሉበትም ገልጸዋል።
የአባላቱ ቁጥር ውስን የሆነው ገበያው ሥርዓት ያለውና ፍትሃዊ እንዲሆን ለማድረግ ነው ብለዋል።
ምርት ገበያው ከአራት ዓመታት በፊት ሥራውን ሲጀምር የመሥራች አባላቱ ቁጥር 100፣ የአባልነት ወንበር ቋሚ ዋጋም 50 ሺህ ብር እንደነበር ዶክተር እሌኒ አስታውሰዋል።
ምርት ገበያው በአዲስ አበባ በአንድ መጋዘንና በ67 ቋሚ ሠራተኞች ሥራ እንደጀመረ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 17 ቦታዎች 55 መጋዘኖችና ከ600 በላይ ቋሚ ሠራተኞች እንዳሉት መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡