የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የሰራተኞች መኖሪያና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋም ግንባታ ርክክብ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2004/ዋኢማ/– በአፋር ክልል እየተገነባ ላለው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የሰራተኞች መኖሪያና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ሁለተኛው ምዕራፍ የተቋማት ግንባታ ተጠናቆ ርክክብ መጀመሩን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ።     

ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ምትኩ ሀበነ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ግንባታቸው ተጠናቆ ርክክብ እየተካሄደባቸው ያሉት 115 ህንፃዎችን ናቸው።

በፕሮጀከቱ በሁለተኛው ምዕራፍ በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር 499 ህንፃዎችን ገንብቶ ለማስረከብ አቅዶ 115 ህንፃዎችን በማጠናቀቅ ርክክቡ ተካሂዷል።

ቀሪዎቹን ህንፃዎች በማጠናቀቅም በተያዘው ወር መጨረሻ ላይ ለማስረከብ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ መንገድ፣ መብራትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችንም ግንባታው እንደሚያካትት ተናግረዋል።

በሁለቱም ምዕራፍ የሚገነቡት 9ሺ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ40ሺ በላይ ለሚሆኑ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች ለመኖሪያነት ያገለግላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

በግንባታው ላይም 300 የሚሆኑ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ማህበራት እንደተሳተፉ ጠቁመው፤ ይህም የአካባቢው ህብረተሰብ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርግ በማስቻሉ በኩል የተሳካ ስራ መስራት አስችሏል ብለዋል።

እንዲሁም ፕሮጀክቱ በቀጣይም በከሰም ለሚገነባው የስኳር ፋብሪካ 3ሺ የሰራተኞች መኖሪያ ህንፃዎችን ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁን አስታውቀው፤ ግንባታውን ለመጀመር የዲዛይን ቦታዎችንና ለግንባው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የመለየት ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በከሰም የሚገነባው የመኖሪያ ቤቶች ህንፃ ፕሮጀክትም ከ3ሺ እስከ 5 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ዋና ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

በተንዳሆ ያጋጠሙ ችግሮችን ተቋቁሞ ስራውን በድል ማጠናቀቁ በከሰም ለሚካሄደው የቤቶችና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ስኬት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመው፤ ይህም የስኳር ኮርፖሬሽን የያዘውን ራዕይና ለሀገር ልማት የሚሰጠውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት ሰራተኛው ከወዲሁ እንዲዘጋጅ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።