ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅና ስፌት ኤክስፖ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 17 2004/ዋኢማ/ – የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው የደረሰበትን ደረጃና በዘርፉ ያለውን እምቅ ሀብት ለማስተዋወቅ የሚያስችል “የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅና ስፌት ኤክስፖ 2004” ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 4 የሚካሄደው ኤክስፖ ገበያና የምርት ግብዓቶችን በማስተሳሰር፣ አምራቾችና ሸማቾችን በማገናኘት በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

በኤክስፖው ላይ በርካታ አምራቾችና የግብዓት አቅራቢዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም በኤክስፖው ላይ ይሳተፋሉ ብለዋል።

ከኤክስፖው ጎን ለጎን ዘርፉን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና በተለያዩ ተቋማት የሚቀርቡበት አውደ ጥናቶች እንደሚካሄዱ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የተመረጡ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች እንደሚጎበኙና በተለያዩ ዲዛይነሮች  መካከል ውድድሮች እንደሚያካሄዱም ተናግረዋል።

ኤክስፖውን በየዓመቱ በቀጣይነት አጠናክሮ ለማካሄድ እቅድ እንዳለ ጠቁመው፤ የዘንድሮው ኤክስፖም በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ገልፀዋል።

ኤክስፖውን የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ቪሌጅ አድቬንቸር ፕሌይግራውንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በጋራ በመሆን እንደሚያዘጋጁትም ተጠቁሟል።

የአገሪቱ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ከ70 አመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም የዕድሜውን ያህል ዕድገት ሳያስመዘግብ መቆየቱን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።