ኮርፖሬሽኑ የሜይሶ-ድሬዳዋ-ደዋሌ የባቡር መስመርን ለማስገንባት የግንባታ ውል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ታህሳስ 7 ቀን 2004 (ዋኢማ) – የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የሚዘልቀው የ656 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታ ሁለተኛው አካል የሆነውን ከሜይሶ-ድሬዳዋ -ደዋሌ የሚዘልቀውን የ339 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ለማስገንባት ከቻይናው የሲቪል ምህንድስና ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር የግንባታ ውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
 
የውል ስምምነቱ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ጌታቸው በትሩ እና በቻይናው የሲቪል ምህንድስና ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ፕሬዝዳንት ዩዋን ሊ መካከል ተፈርሟል፡፡
 
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ጌታቸው በትሩ እንደገለፁት ኮሜይሶ-ድሬዳዋ ደዋሌ ያለው ፕሮጀክት መልክዓ ምድራዊ አቀማማጡ ለባቡር መስመር ምቹ በመሆኑ በአንፃራዊነት ቀድመው ከሚደርሱ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ይሆናል፡፡ ከወደብ ያለው ቅርበትም ግብአቶች በወቅቱ እንዲደርሱ አጋዥ ይሆናል፡፡
 
ሶስት አመታት ከስድስት ወር በሚዘልቀው የመጀመሪያው ዙር ሀገራዊ የባቡር መስመር ዝርጋታ ከ350 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሊሳተፉ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ በዚህ ዙር 2300 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታ እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡
 
የሜይሶ-ድሬዳዋ-ደዋሌ ፕሮጀክት አጠቃላይ ወጭ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ይደርሳል፡፡በፕሮጀከቱ ግንባታ ላይ የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እስከ 60 በመቶ የሚደርስ በመሆኑ ግን የፕሮጀክቱ ግንባታ አነስተኛ በሚባል መልኩ በብድር እንደሚሰራ ነው የገለፁት፡፡
 
ፕሮጀክቱን ለመጀመር የሚያስችሉ የካሳ ክፍያ ጉዳዮች በአፋጣኝ መጠናቀቅ አለባቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ከተፈቱ ኮርፖሬሽኑ ቀን ከሌሊት በመስራት ፕሮጀክቱን በጊዜው ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡
 
የቻይናው የሲቪል ምህንድስና ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ፕሬዝዳንት ዩዋን ሊ በበኩላቸው ይህንን ፕሮጀክት በጊዜ ገደቡ አጠናቀው እንደሚያስረክቡ ገልፀዋል፡፡ (ERTA)