ሴቶች ሊታይና ሊመዘን የሚችል ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2004/ዋኢማ/– ሴቶች መነሳሳቱና ወኔው ካላቸው መብቶቻቸውን በማስከበር ሊታይና ሊመዘን የሚችል ለውጥ ማምጣት የማይችሉበት ምክንያት እንደሌለ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቀዳማዊ እመቤት አዜብ መስፍን አስታወቁ።

ቀዳማዊ እመቤት አዜብ መስፍን ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ  የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አመታዊ ስብሰባ ላይ እንደገለፁት፤ የሴቶችን ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መንገድ ለማሳደግ ሴቶች ህገ-መንግስቱ የሰጣቸውን መብት በመጠቀም ከፍተኛ ወኔና መነሳሳትን ሰንቀው በመደራጀት ሊሰሩ ይገባል።

ሴቶች መነሳሳቱና ወኔው ካላቸው በመደራጀት ረዥም ርቀት ለመጓዝ፣ በስራቸው አመርቂ ውጤት ለማምጣትና አንፀባራዊ የሆነ ድል ለማስመዝገብ የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።

ሴቶች በትግላቸው ባገኙት መብትና ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻልም “የሴቶች ልማትና ለውጥ ፓኬጅ” ተቀርፆ በመላው ሀገሪቱ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፤  ፓኬጁን ተግባራዊ በማድረግ ለውጦችን ማየት መቻሉን ተናግረዋል።

በተለይም በስነ-ፆታ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመው፤  የሴት ልጅ ግርዛት፣ የእናቶች ሞት መቀነስ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቆምና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከሉ በኩል መልካም የሚባል ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።

ሆኖም በከፍተኛ ወኔ የታጀበ እንቅስቃሴ ቢደረግ ከዚህም በላይ ለውጥ ማስመዝገብ ይቻል እንደነበረ ጠቁመው፤ አመራር ላይያሉ ሴቶችም ታሪካዊ ሚናቸውን በመጫወት የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚሰፋበት መንገድ ላይ በፅኑ አቋም በመመስረት እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል በማለት አሳስበዋል።

በመሆኑም የሀገሪቱን ሴቶች ችግር ለመቅረፍ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ከፊታቸው ያለውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ በሚደረገው ፍልሚያ አስፈላጊውን ቁርጠኝነት ሊያሳዩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ለውጥ በቂ ነው ለማለት እንደማይቻል የገለፁት ቀዳማዊ ፕሬዚዳንቷ፤  አመራር ላይ ያሉ ሴቶች ይበልጥ ለለውጡ መነሳሳት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።  

በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪና የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፤ የሴቶችና የወጣቶች ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው ደረጃ ለማሳለጥ ሴቶችና ወጣቶች በተደራጀ መንገድ በዕድሉ ሊጠቀሙና በዚሁ መንገድ ዕድሉን ይበልጥ በማስፋትም መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሴቶች በተናጠል ከሚያደርጉት ልማታዊ እንቅስቃሴ ይልቅ ተደራጅተው ቢንቀሳቀሱ ውጤታማ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ ከፍተኛ አቅምና ግንባታ የሚፈጥርላቸው እንደሚሆን ተናግረዋል።

ስለአደረጃጀቱ ስኬታማነት ሲወሳም በየደረጃው ስለሚኖርና መኖር ስለሚገባው የአመራር አቅምና አመለካከት አንድ ላይ ሲቃና ትክክለኛ  የተግባር ምንጭ ይሆናል ብለዋል።

በዚህ ረገድም እስከዛሬ የተደረጉ ጥረቶች፣ የተገኙ ስኬቶች፣ የሚስተዋሉ እጥረቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች የእያንዳንዱ አመራር ድርሻን በመፈተሽ ከእጥረቶችም ከስኬቶችም ልምድ በመውሰድ በተሻለ ሁኔታ በመንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቁመው፤  ይህም የአምስት አመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት የተቀመጠውን ሰፊ ዕቅድ ወደ ተጨባጭ ተጠቃሚነት መለወጥ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል።

የእቅዱ የስኬት መለኪያዎች ከሆኑት የማዕዘን ድንጋዮች አንዱ የሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው በማለት አመልክተዋል።

በመሆኑም ትርጉም ያለው ንቅናቄ ከታች እስከ ላይ ማቀጣጠል እንደሚገባ ገልፀው፤ በዚህ ረገድ ፌዴሬሽኑ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ የመንግስት ድጋፍ እንደማይለየው አረጋግጣለሁ ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትምህርት፣ በጤናና በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ውጤታማነታቸውን ማሳደግ ይቻላል ብለዋል።

የሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ሚኒስትር ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ በበኩላቸው፤ የሴቶች ተጠቃሚነትን ለማሻሻልና ለማሳደግ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመለየት ወደ ሁሉም የሀገሪቱ ክልሎችና የመስተዳደር ከተሞች ማስፋፋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለዚህ ተግባራዊነትም ሴቶች በጠንካራ አመራር ታቅፈው ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል በማለት ተናግረዋል።

በስብሰባው ላይም የትግራይ ክልል ምርጥ ተሞክሮ የቀረበ ሲሆን፤  ስብሰባው ለሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።