አውስትራልያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ አስታወቀች

አዲስ አበባ፤ጥር 19 2004 /ዋኢማ/– አውስትራልያ ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቁ።

በአድስ አበባ የአውስትራልያ ኤምባሲ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ እንደተናገሩት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር ፍላጎት አላት።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ በሆነችው በአዲስ አበባ አገራቸው  ኤምባሲ መክፈቷም  የሁለቱን አገራት ወዳጅነት ያጠናክራል። በንግድ፣በኢንቨስትመንት፣በሠላምና ፀጥታ እንዲሁም በከባቢ አየር ለውጥ እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራትም ያስችላል።

ኤምባሲው አውስትራልያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠናክር እንደሚያግዛትም ኬቪን ሩድ ተናግረዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አውስትራልያ በአዲስ አበባ ኤምባሲ መክፈቷ አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ከማሳየቱም

በላይ ለአፍሪካ ያላትን የረጅም ጊዜ አጋርነት ያንፀባርቃል።
በኤምባሲው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ አምባሳደሮች፣ዲፕሎማቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።