አፍሪካ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍተኛ ደረጃ እያገኘች ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2004 (ዋኢማ) – አፍሪካ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍተኛ ደረጃ እያገኘች መምጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 26ኛው ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት/ኔፓድ/ የመሪዎች ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረበት ወቅት ባደረጉት ንግግር አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት አቋም ካለፉት 10 አመታት ጋር ሲነፀፀርም የተሻለ ቦታ ላይ ትገኛለች፡፡

ኔፖድ ከተመሰረተ ሁለተኛውን አስርት ዓመታት በዘንድሮው የአውሮፓውያን ዓመት እንደጀመረ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኔፓድ የመጀመሪያው አስርት አመታት ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት፣ ፀጥታና ደህንነት እንዲሁም ሠላማዊ የዲሞክራሲ ሂደት በጥልቅ መሠረት ላይ የተጣለበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በአህጉሪቱ ፖለቲካዊ የጋራ መግባባት በመፈጠሩ፣ የተጣጣመ ፖሊሲ በመኖሩና ኔፓድን ተጠቃሚ የሚያደርግ የተቀናጀ ስራና ዘርፈ ብዙ የምክክር መድረኮች የተካሄዱበት ወቅትም ነበር ብለዋል፡፡

በተለይም በአውሮፓ ያጋጠመውን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ቀውስ አፍሪካን በመጪዎቹ አመታት የምታስመዘግበውን እድገት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል መገመቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቋቋም አህጉሪቱ ከቀደመው አስር አመት ይልቅ የተሻለ ዝግጅት ማድረጓንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ካለፉት ዓመታት የተሻለ እድገት ለማስመዝገብ እንደምትችልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው በዚህ ረገድም ኔፓድ ለአህጉሪቱ ልዩ የልማት መርሃ ግብር በመንደፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዚሁ የመሪዎቹ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ አህጉራዊ የመሠተ ልማት ስትራተጂዎች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመው ይህም የአፍሪካ የመሠረተ ልማትየመሠረተ ልማት ፕሮግራም ላይ በመመስረት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት ከቡድን 8 እና 20 የአውሮፓን 2012 እይታ አንፃርና ከተባበሩት መንግስታት ትብብር አኳያም መቃኘት እንዳለበት አሳስበባል፡፡
ኔፓድንና አፍሪካ ሕብረትን ለማዋሃድ የተጀመረው ፕሮግራም እንቅስቃሴም በስብሰባው ላይ እንደሚቃኝ ጠቁመው ለስኬታማነቱም የስብሰባው ተሳታፊዎች ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለውህደቱ ስኬታማነት የተቋቋመው የአፍሪካ ሕብረት ቴክኔካል ኮሚቴ መዋቅራዊ አደረጃጀቱ ከኔፓድ አጀንዳ ጋር የተጣጣመና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡

ኔፓድ በአባል አገራት መካከል ልምድ ለመጋራትና በጋራ ለመስራት እንዲሁም የአፍሪካን ሕዳሴ ለማምጣት የመሠረት ድንጋይ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት 10 ዓመታት ለአህጉሪቱ ልማትና ለአጋሮች ትብብር የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ኔፓድ የተመሰረተው እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2001 ሉሳካ ዛምቢያ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡