የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ርዕሳነ ብሄራት፣የአገሮችና የመንግሥታት ተወካዮች በተገኙበት ተከፈተ

አዲስ አበባ፤ጥር 21 2004 /ዋኢማ/– የአፍሪካ ኅብረት 18ኛው የመሪዎች ጉባኤ የ53 የአፍሪካ አገራት ርዕሳነ ብሄራት፣የአገሮችና የመንግሥታት ተወካዮች በተገኙበት በድምቀት ተከፈተ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ዤን ፒንግ ጉባኤውን ሲከፍቱ እንዳሉት አፍሪካ አሁንም ድረስ ያልተወገዱ ችግሮች ያሉባት አህጉር ብትሆንም፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላት ተጽእኖ ግን እያደገና እየሰፋ መጥቷል።

በአፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ግጭቶችና አለመግባባቶች እንደሚስተዋሉ አብራርተው፣ አህጉሪቱ በራሷ ጥረት ለችግሮቿ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናት ብለዋል።

በአፍሪካ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም አህጉሪቱ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ስለመሆኗም ዶክተር ፒንግ ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ መናጋት በደረሰበት በአሁኑ ወቅት አፍሪካ ግን በተቃራኒው በዓመት ከአምስት እስከ ስድስት በመቶ የደረሰ የምጣኔ ሐብት እድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሆነችም ተናግረዋል።

ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከስድስት በመቶ በላይ አመታዊ የምጣኔ ሃብት እድገት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ጥቂት አገሮች ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት እንዳስመዘገቡም ገልጸዋል።

ዶክተር ፒንግ እንዳብራሩት አፍሪካ ልክ ቻይናና ሕንድ ከጥቂት አሥርት ዓመታት በፊት እንዳደረጉት ሁሉ፤ የላቀ የምጣኔ ሃብት እመርታ የማምጣት ሰፊ አቅም አላት።

አፍሪካ ከ10 ዓመታት በፊት እንደ ”ዘ ኢኮኖሚስት” መጽሔት በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ የነበራት ምስል ጨለምተኛና ተስፋ ቢስ እንደነበር አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት እነዚህ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አህጉሪቱን የሚገልጹት ግን ከዚህ ቀደም እንደነበረው ተሰፋ ቢስና ጨለምተኛ ሳይሆን፤ አፍሪካ እያደገችና ገናና እየሆነች መምጣቷን ነው ብለዋል።

ሊቀመንበሩ እንዳብራሩት በአህጉሪቱ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ግጭቶችና አለመግባባቶች እየቀነሱና በምትኩም ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ መምጣቱ፣ዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር መጠናከር፣ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ መሻሻል በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን ተደማጭነትና መልካም ገጽታ አሳድጎታል።

አፍሪካ ያሉባትን ችግሮች ለመፍታት በራሷ መንገድ ከፍተኛ ጥረቶችን እያደረገች ብትሆንም፤ አህጉሪቱ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን ስትራቴጂካዊ ትብብር አጋርነትንም የበለጠ ታጠናክራለች።

የመሪዎቹ ጉባዔ ልዩ እንግዳ የሆኑት የቻይና የፖለቲካ ምክክር ጉባኤ ብሄራዊ ኮሚቴ ሊቀመንበር ጂያ ኩዊንግሊን እንዳሉት በአፍሪካና በቻይና መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ግንኙነት እየተጠናከረና እያደገ መጥቷል።

የቻይናና የአፍሪካ አዲሱ ስትራቴጂያዊ የትብብር ግንኙነት በሁለቱ አካላት መካከል ያለው ግንኙነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣በንግድና በባህል ያለውን ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታልም ብለዋል።

ቻይና ምንጊዜም ቢሆን የአፍሪካ መልካም ወዳጅና አጋር ሆኗ እንደምትጥቀል የገለጹት ሚስተር ጂያ፣የሁለቱን ወገኖች ወዳጅነት ማጠናከርና የጋራ የልማት አጀንዳዎች ማሳደግ የአገራቸው ዋነኛ የውጭ ፖሊሲ የማዕዘን ድንጋይ መሆናቸውን ለመሪዎቹ አስረድተዋል።

ቻይና በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የአፍሪካ ኅብረትን አቅም ለማጠናከር የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግም ይፋ አድርገዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን በበኩላቸው አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍተኛ ተደማጭነትን እያገኘች መምጣቷን መስክረዋል።

በአህጉሪቱ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የአፍሪካ ህብረትና የኅብረቱ አካል የሆኑት ድርጅቶች እያበረከቱ ያሉትን ጥረትም አድንቀዋል።

ለአብነትም በኮትዲቯር፣በሊቢያ፣በቱኒዚያ፣በግብፅ፡ በሶማሊያና በሌሎችም አገሮች ያለውን እንቅስቃሴ አንስተዋል።

ሚስተር ባን እንዳሉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት መካከል ያለው ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከርም ድርጅቱ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረትና ተመድ በዳርፉር፣በሶማሊያና በጊኒ እያደረጉ ያሉትን የጋራ የዲፕሎማሲና የሰላም ማስከበር የትብብር ጥረትም የበለጠ እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል።

በሁለቱ ተቋማት መካከል በችግሮች አፈታት ዙሪያ የአቋም ልዩነቶች ቢኖሩም፤ ወደፊት በጋራ ለሚያከናውኗቸው እንቅስቃሴ ልዩነቶችን ለማስወገድ በትብብር መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በአፍሪካ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት በ25 አገሮች ውስጥ ፕሬዚዳንታዊ፣የፓርላማና ና የአካባቢያዊ ምርጫዎች እንደሚካሄዱ የገለጹት ዋና ጸሐፊው ሁሉም ምርጫዎች ግልጽ፣ትክክለኛና ሁሉንም አሳታፊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በጋራ ለመሥራትም ጥሪ አቅርበዋል።

በቱኒዚያ የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም በዴሞክራሲያዊነቱ ለሌሎች አገራት ሊጠቀስ የሚገባ ነው ሲሉ ባን አሞካሽተውታል።

ተመድ ከኅብረቱ ጋር በጋራ በመሆን በዓለም አቀፍ ሰላምና ጸጥታ ረገድ ያለውን የትብብር ግንኙነትም የበለጠ ማጠናከርና ማስፋት ይፈልጋል።

በጉባኤው ላይ አዲስ የተመረጡት የቱኒዚያው ፕሬዚዳት ሞንሴፍ ማርዙኪና የሊቢያ የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብዱራህማን ኤል ኪባም ንግግር አድርገዋል።

ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የመሪዎቹ ጉባኤ በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የዘገበው ኢዜአ ነው።