ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከሦስት አገሮች የልዑካን ቡድኖች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 21 2004 /ዋኢማ/ – ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፣ ከስዊድንና ከኢራን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል በሚያስችላት ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከአገሮቹ የልዑካን ቡድኖች ጋር ተወያዩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ጠንካራና መልካም ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ላይ ውይይት አድርገዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ እያሳየች ባለው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት የአሜሪካ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን በሚያፈሱበት ሁኔታ ላይም ምክክር አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መከበር የምትጫወተው ጉልህ ሚና የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አድንቀዋል።

ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሚያደርጉት ከፍተኛ ድጋፍ ላይም መክረዋል።

የሶማሊያ የሰላም ሁኔታን ለማረጋገጥ የአፍሪካ ኀብረት፣ ኢጋድ፣ ኢትዮጵያና የአካባቢው አገሮች እያደረጉት ባለው ጥረት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከባለሥልጣናቱ ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ ከስዊድን ጋር ያላት የትብብር ግንኙነት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከአገሪቱ የልዑካን ቡድን ጋር ተነጋግረዋል።

እንዲሁም ከኢራን ጋር ባለው ግንኙነት ዙሪያና ወደፊትም ተጠናክሮ በሚቀጥልበት አቅጣጫ ላይ ከአገሪቱ የልዑካን ቡድን ጋር መመካከራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኔ ገብረክርስቶስን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።