አገሮች ለዘላቂ ልማት ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጥ የዕድገት አቅጣጫ እንዲከተሉ ዋና ፀሐፊው ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2004/ዋኢማ/ – አገሮች ለዘላቂ ልማት ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጥ የዕድገት አቅጣጫ መከተል እንደሚገባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አስገነዘቡ፡፡

ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ዓለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ፓናል ሪፖርት ይፋ በሆነበት ወቅት እንዳሳሰቡት፤ አገሮች ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ የዕድገት አቅጣጫ መከተል ይጠበቅባቸዋል፡፡

የዓለም የሥነ-ምህዳር በከፍተኛ ጫና ሥር በወደቀበትና የሰው ልጆች የተፈጥሮ ሃብት ፍላጎት በእጅጉ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተዳምሮ ዘላቂ ልማትን መከተል የግድ ያደርገዋል ብለዋል።

የድርጅቱ አባል አገሮችና ባለድርሻ አካላት መጪው ዓለም ልማት ዘላቂነት ያለው እንዲሆን ለማስቻል በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ባን አሳስበዋል፡፡

ታዳጊ አገሮች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ የሚያስችል የገንዘብ፣ የቴክኒክና የቴክኖሎጂ እገዛ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

በፓናሉ የቀረበው ሪፖርትም በመጪው ሰኔ 2004 በብራዚል ሪዮ ዲጄኒሪዮ ከተማ ለሚካሄደው የድርጅቱ የዘላቂ ልማት ኮንፈረንስ በግብዓትነት እንደሚውል አመልክተዋል፡፡

ዘላቂ ልማት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የዓለም ማኅበረሰብ ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ በጋራ እንዲንቀሳቀስ ዋና ፀሐፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የድርጅቱ የዘላቂ ልማት ከፍተኛ ፓነል ሪፖርት “የማይበገር ሕዝብ፤ የማትበገር ፕላኔት-ለመጪው ዘመን የተሻለ ምርጫ” በሚል ጭብጥ አዲስ አበባ ውስጥ ይፋ ሆኗል፡፡

የፓነሉ ተባባሪ ሰብሳቢ የፊንላንድ ፕሬዚዳንት ሚስስ ታርጃ ሃሎኔን በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሕዝብን ማዕከል አድርጎ ማቀድ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የዓለም ኅብረተሰብ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንዲቻል ፍትሃዊነትን በማስፈን ድህነትን ለማስወገድ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራበትም ጠይቀዋል፡፡

ዘላቂ ልማት ሲታሰብ ሴቶችን የማብቃትና በኢኮኖሚ መስክ ከፍተኛ ሚና እንዲኖራቸው ማረጋገጥ ተገቢነት እንዳለው አድርገዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትና የፓነሉ ተባባሪ ሰብሳቢ ጃኮብ ዙማ በበኩላቸው፤ ዓለም በኢኮኖሚ ቀውስ መታመሷ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ፖሊሲ አመንጪዎች ቀውሱን ለመታደግ የሚያስችል ዘላቂ ልማት መተለም እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ረገድ አገሮች በሚከተሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዘላቂ ልማትን ማካተት የሚያስችላቸውን 56 የመፍትሄ ሃሳቦች በሪፖርቱ መቅረቡን አመልክተዋል ሲል የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።