ሀዋሳ፤ ታህሳስ 16/2004 (ዋኢማ) –በደቡብ ክልል ከ 20 ሺህ በላይ አባወራ አርብቶአደሮችን በመንደር ለማሰባሰብ የሚያስችለውን መሰናዶ ማጠናቀቁን የክልሉ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነትና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጌቱ ዓለሙ ለዋልታ እንዳስታወቁት አርብቶአደሮችን በመንደር የማሰባሰቡ ሥራ የሚካሄደው በደቡብ ኦሞ እና በቤንች ማጂ ዞኖች ነው::
የመንደር ማሰባሰቡ የሚካሄደው በዞኖቹ በሚገኙ በዳሰነች@ በሐመር @ በኛንጋቶም @ በፀማይ @ በማሌ @ በሰላማጎ @ በቤሮ @ በማጂ @ በሜኒትሻሻ እና በሜኒትጎልዲያ ወረዳዎች መሆኑን ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪው አብራርተዋል::
ቢሮው ባለፉት ሦስት ወራት በሰፈራ ፕሮግራም ለመካተት ፍቃደኛ የሆኑ አባወራዎችን መለየቱን የገለጹት የሥራ ሂደቱ አስተባባሪ ከተያዘው የበጀት ዓመት አጋማሽ ጀምሮ አርብቶአደሮቹን የማስፈር ሥራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል ::
እንደ አቶ ጌቱ ማብራሪያ አርብቶአደሮቹ የሚሰባሰቡባቸው መንደሮች ተፋሰሶችን ተከትለው የተዘጋጁ በመሆናቸው ቀደም ባሉት ጊዜያት አርብቶአደሩ በዝናብ እጥረት ምክንያት ግጦሽ ፍለጋ ከቦታ ቦታ በመጓጓዝ ይደርስበት የነበረውን ድካም ያስቀራሉ፤ በአንድ አካባቢ ተረጋግቶ የመኖር ባህልን እንድያዳብርም ያስችላል ::
ለሠፈራ በተመረጡት አካባቢዎች የመኖሪያ ቤቶች፣ የውሃና የጤና አገልገሎቶች የተዘጋጁ ሲሆን ቀሪ የመሠረተ ልማት ተቋማትን በሂደት የማሟላት ሥራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።
ከመሠረተ ልማት ሥራዎች በተጨማሪ ለሠፋሪ አባወራዎች በነፍስ ወከፍ ሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር የእርሻ መሬት @ የግብርና መገልገያ ቁሳቁሶችና ግበዓቶች እንደሚቀርቡላቸው የሥራ ሂደት አስተባባሪው ገልጸዋል::
በደቡብ ክልል በ 2003 የበጀት ዓመት በመንደር የተሰባሰቡ 10 ሺህ 995 አባወራ አርብቶአደሮች በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ኑሮ በመምራት ላይ እንደሚገኙ ከሥራ ሂደት አስተባባሪው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።