ኢትዮጵያ በሃይል አቅርቦት ዘርፍ ምስራቅ አፍሪካን ለማስተሳሰር እያደረገች ያለችው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16 ቀን 2004 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያ በሃይል አቅርቦት ዘርፍ ምስራቅ አፍሪካን ለማስተሳሰር እያደረገች ያለችው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ኢትዮ-ኬንያን በኤሌክትሪክ ሃይል ለማስተሳስር የሚያስችል ስምምነት በቅርቡ በሁለቱ አገራት መካከል መደረጉንም ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ አመልክተዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ወደ ውጭ ለመላክና ለማስፋፋት እያደረገች ያለችው ጥረት ስኬታማ እየሆነ መጥቷል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምታመነጨውን ኃይል በመሸጥ በአህጉሩ ኢኮኖሚያዊ ትስስር መፍጠር እንዲቻል ሴክተሩን በስፋት እያለማች ነው ብለዋል ፡፡

በቅርቡ ኢትዮ ኬንያን በሃይል ማሰተሳሰር የሚስችሉ ጥናቶች በመጠናቀቃቸው በሁለቱ አገራት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት ለኬንያ 400 ሜጋ ዋት ሃይል ለማቅረብ ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኃይል ማመንጨት፣ ማሰራጨትና ማከፋፈል አኳያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ያስታወቁት ሚኒስትሩ የኢትዮ ኬንያን በሃይል የማስተሳሰር ሰራን ለማስጀመር መንግስታቱ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ምህረት ደበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮ-ኬንያ የሃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት የቅድመ አዋጭነት፣ የአዋጭነትና የዲዛይን ስራ ተጠናቆ ስራውን ለማስጀመር ስምምነት ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይል ሴክተር በአስር አመት ማስተር ፕላን እቅድ መሰረት የሃይል አቅርቦትና ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ትንትና የተከናወነው ከአለም አቀፍና ከአገር አቀፍ የኢነርጂ ገበያ እድገት፣ አቅርቦትና ፍላጎት መጣጣም ጋር በተቀናጀ መልኩ ነው፡፡

ጥናቱ በአለም አቀፍና የአገር ውስጥ ባለሙያዎች የተደረገ ሲሆን የአካባቢ ጥበቃ ጥናቶች መሰረት በማድረግ አለም አቀፍ ደረጃውን እንዲያሟላ ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በአለም አቀፍ አበዳሪዎች ትልቅ ግምት የተሰጠው ነው ያሉት አቶ ምህረት በተለይ የአለምና የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የጀርመን ፋይናንስ ተቋምንና የፈረንሳይ ልማት ትብብርን ትኩረት አግኝቷል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ስራውን ለማስጀመር በኢትዮጵያ በኩል የአለምና የአፍሪካ ልማት ባንክ በኬንያ ወገን ደግሞ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የፈረንሳይ ልማት ትብብርን ጨምሮ ሁለቱም ባንኮች የሚፈለገውን የ1 ቢሊዮን ብር በጀት መድበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሁለቱን አገራት በእኩልነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን የኢኮኖሚ ትብብርና የፖለቲካ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ (ኢዜአ)