የአረብ ኤሚሬትስ መንግስት 26 የባጃጅ አምቡላንሶችን በእርዳታ ሰጠ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 17 2004 /ዋኢማ / – በኢትዮጵያ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሁሉም የሀገሪቱ ወረዳዎች የአምቡላንስ አገልግሎት ለማዳረስ እየተሰራ ሙሆኑን የጤናጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
የተባበሩት የአረብ ኤሚሬትስ መንግስት በበኩሉ በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ለማገዝ 26 የባጃጅ አምቡላንሶችን በእርዳታ ሰጧል።
 
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም እንደገለፁት በኢትዮጵያ ባሉ 800 ወረዳዎች የሚዳረሱ የ800 አምቡላንሶች ግዢ ተፈጽሞ ወደ ሀገር ውስጥ በመጓጓዝ ላይ ናቸዉ።
በእስካሁኑ ሂደትም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል 50 አምቡላንሶች ለወረዳዎች ተሰራጭተዋል፡፡

ዶክተር ቴዎድሮስ እንዳሉት የእናቶች እና የህጻናት ሞትን ለመቀነስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አምቡላንሶቹ የበኩላቸውን እገዛ ያደርጋሉ።
 የተባበሩት የአረብ ኤሚሬትስ መንግስት በበኩሉ ለጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ያግዛሉ የተባሉና ከጤና ኬላ ወደ ጤና ጣቢያ ህሙማንን የሚያመላልሱ 26 የባጃጅ አምቡላንሶችን በእርዳታ ሰጧል፡፡

በኢትዮጵያ የአረብ ኤሚሬትስ አምባሳደር ዶክተር የሱፍ ኢሳ ሃስ አል ሳብሪ በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት በቀጣይም እንደሚያግዙ ገልጸዋል።አምባሳደሩ አገራቸዉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የባጃጅ አምቡላንሶችን ጨምሮ ሌሎች የጤናውን ዘርፍ የሚደግፉ እርዳታዎችን እንደምታደርግም ጠቁመዋል ።

በእርዳታው የተገኙት ባጃጆች አጠቃላይ ወጪ ከአንድ ሚሊዩን ብር በላይ መሆኑን እና ከከተማ ውጪ ለሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች በሚያመች መልኩ መገጣጠማቸዉን የዘገበዉ ኢ.ሬ.ቴ.ድ ነዉ፡፡