በደቡብ ክልል 16 መንደሮች በቱሪስት መስህብነት ተከለሉ

ሀዋሳ፤ታህሳስ 18 2004/ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል 16 ባህላዊ መንደሮች በቱሪስት መስህብ ሥፍራነት እንዲከለሉ ማድረጉን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ::

በቢሮው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ ወይዘሪት ንጋት ማቲዮስ  እንዳስታወቁት ባህላዊ መንደሮቹ በቱሪስት መስህብነት ሊከለሉ የቻሉት በባለሙያዎች አማካኝነት በመንደሮቹ ላይ ተከታታይ ጥናቶች ከተካሄዱ በኃላ ነው ::

ለቱሪስት መስህብነት የተከለሉት መንደሮች የኮንሶ፣ የጉራጌ፣ የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የከንባታ፣ የጠንባሮ፣ የኮንታ እና የደራሼ  ብሄረሰቦች በመኖሪያነት የሚገለገሉባቸው መሆናቸውን ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪዋ አብራርተዋል ::

መንደሮቹ በቱሪስት መስህብነት ሊመረጡ  የቻሉት በጥንታዊ የቤት አሠራራቸው እና በውስጣቸው በሚገኙ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶቻቸው እንዲሁም መንደሮቹ ባላቸው ማራኪ የመልካዓ ምድራዊ አቀማመጥ መሆኑን ተናግረዋል ::

የመንደሮቹ በቱሪስት መስህብነት  መከለል በክልሉ የሚገኙ ሕዝቦች ባህላዊ እሴቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠራቸውም በላይ ወደ ክልሉ ለሚመጡ ጎብኚዎች በአማራጭ የመስህብ ሥፍራነት ለማገልገል እንደሚያስችሉ  አመልክተዋል ::

ማህበረሰቦቹ መንደሮቹን በእንክብካቤ በመያዝ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር ለመዘርጋት ቢሮዉ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አስተባባሪዋ ተናግረዋል ::

የክልሉ መንግሥት በሚቀጥሉት  አምስት ዓመታት የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና ተፍጥሯዊና ታሪካዊ ሥፈራዎችን በመጠበቅና በመንከባከብ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚያገኘውን ገቢ በእጥፍ ለማሳደግ ዕቅድ ይዞ  እየሠራ ይገኛል::

በ2003 የበጀት ዓመት ክልሉን ከጎበኙ የአገር ውስጥና የውጪ አገር ቱሪስቶች ከ 93 ሚሊዮን 718 ሺህ ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል::