አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20 2004 /ዋኢማ/ – አዲስ የሚዘረጋዉ የባቡር ሀዲድ መስመር ለሚያልፍበት ጣቢያ ግንባታ የሚውል ከ100 ሄክታር በላይ መሬት ማዘጋጀቱን የሞጆ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ ።
የከተማዉ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሲሳይ በቀለ እንደገለጹት አስተዳድሩ ለባቡር ጣቢያ ግንባታ የሚዉለዉን መሬት ያዘጋጀዉ ከኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ነዉ ።
የከተማዋ አስተዳደር የባቡር ሃዲዱን ግንባታ ለማፋጠን እንዲቻል የከተማዋን ህዝብ በማወያየትና በማሳመን ለግንባታዉ የሚያስፈልገዉን መሬት የማዘጋጀት ስራ እያካሄደ መሆኑን አስታዉቀዋል ።
በሞጆ ከተማ አዲስ የሚገነባዉ ባቡር ጣቢያ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ እንዲሁም ከአዲስ አበባ -ሞያሌ -ኬንያ ለሚዘልቀው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዋንኛ ማሳለጫ በመሆን እንደሚያገለግል ከንቲባዉ ገልፀዋል ።
የባቡር ጣቢያው ከሚያርፍበት አካባቢ ለሚነሱ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ የካሳ ክፍያ በመፈጸም ነዋሪዎችን ከአካባቢው በፍጥነት ለማንሳት በሂደት ላይ መሆናቸዉንም ተናግረዋል ።
እንደ ከንቲባዉ ማብራሪያ የባቡር ጣቢያው መገንባት ለአካባቢው ህዝብና ለሀገር የሚሰጠውን ጥቅም በመረዳት ነዋሪዎች በፈቃደኝነት ከነበሩበት ተነስተዉ ቦታውን እንዲያስረክቡ የማወያየትና የማሳመን ስራ ሲከናወን ቆይቷል።
በግንባታዉ ምክንያት ከይዞታቸዉ የሚነሱት ከ2 ሺህ 100 በላይ ነዋሪዎች አስፈላጊዉ የካሳ ክፍያ የሚፈጸምላቸዉ ሲሆን በግንባታዉ ከ5 ሺህ በላይ ዜጎችም የስራ እድል እንደሚፈጠርላቸዉ አቶ ሲሳይ አስታዉቀዋል ።
የአካባቢዉ ነዋሪዎች በከተማዋና በአካባቢው ለሚከናወኑ ሰፋፊ የመንግስት የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ስኬታማነት እስከአሁን ሲሰጡ የቆዩትን ድጋፍና ትብብር አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉም ያላቸዉን እምነት መግለፃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል ።