ምክር ቤቶች የአስፈፃሚ አካላትን ተግባራት የመቆጣጠር ሚናቸውን አጠናክረዉ መቀጠል አለባቸዉ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21 2004 /ዋኢማ/ – ለእድገትና ትራንስፎርሜሸን እቅዱ ስኬታማነት ምክር ቤቶች የአስፈፃሚ አካላት ተግባራትን የመከታተልና የመቆጣጠር ሀላፊነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ።

የህዝብ  ተወካዮችና  የክልል  ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች የጋራ  መድረክ ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ  ሲጀመር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ እንደተናገሩት የአስፈፃሚ አካላት የሚያወጡአቸውን እቅዶች በየጊዜው ማከናወናቸውን መቆጣጠርና መከታተል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስችላል።

የጋራ የምክክር መድረኩ የህዝብ  ተወካዮችም ሆኑ የክልል  ምክር ቤቶች አባላት፣ የአስፈጻሚ አካላት የሚያወጧቸውን ዕቅዶች አፈጻጸም ለመገምገም የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥርላቸዉ አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ   ተናግረዋል።

በአስፈፃሚ አካላት በኩል የተሰጣቸውን በጀትና ተግባራት በጊዜው ያለመፈፀምና በቋሚ ኮሚቴዎች የሚሰጣቸውን ግብረ መልስ በአፋጣኝ ምላሽ ያለመስጠት ችግር እንዳለ በቢሾፍቱዉ ጉባኤ ተነስቷል።

በምክር ቤቶች ተግባራት ዙሪያ ዜጎች በተገቢው ሁኔታ እንዲሳተፉ አለማስቻልም እንዲሁ።

የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታትም ምክር ቤቶችም ሆኑ የአስፈፃሚ አካላት የጋራ መግባባት ፈጥረው መስራት እንዳለባቸዉ ጥሪ መቅረቡን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል ።