ባለስልጣኑ በ150 ሚሊዮን ብር ወጪ የመንገድ ዲዛይንና ግንባታ ስራ ያከናውናል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21 2004 /ዋኢማ/ – የአዲስ አባባ መንገዶች ባለስልጣን በ150 ሚሊዮን ብር ወጪ የመንገድ ዲዛይን ጥናት፣ ግንባታና የቁጥጥር ስራ ዘንድሮ እንደሚከናወን አስታወቀ፡፡

ከአንድ ተቋራጭና ከተለያዩ አማካሪ ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት ትናንት ተፈራርሟል፡፡

በስምምነት ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተገለጸው በመዲናዋ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ ለአምስት የመንገድ ፕሮጀክቶች የዲዛይን፣ የግንባታና የቁጥጥር ስራ ይከናወናል፡፡

ለፕሮጀክቶቹ በአጠቃላይ 146 ሚሊዮን 992 ሺህ 741 ብር ወጪ እንደሚደረግ ጠቁሞ ከዚህ ወጪ ውስጥ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ለዲዛይን ጥናትና የግንባታ ጥራት ቁጥጥር ይውላል፡፡

በተጨማሪም ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የፊሊጶስ ድልድይና መቃረቢያው መንገድ ግንበታ እንደሚከናወን ገልጾ የፊሊጶስ ድልድይ ዲዛይን ስራ በመጠናቀቁ በዕለቱ ወደ ግንባታ ለመግባት

የሚያስችለውን ጨረታ ያሸነፈው አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ከባለስልጣኑ ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ድርጅቱ 40 ሜትር ርዝመትና 16 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለውን ድልድይ እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመቃረቢያ መንገድ ለመገንባት ስራውን በተቋራጭነት ተረክቧል፡፡

ባለስልጣኑ የሶስት መንገዶች ዲዛይን ጥናትና የግንባታ ቁጥጥር ስራ ለማከናወን ከቤስት ኮንሰልቲግ ኢንጂነርስ ጋር የ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ያህል የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

አማካሪ ድርጅቱ የ8 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር መንገድ የዲዛይንና የቁጥጥር ስራ እንደሚያከናውን በጨረታ ማሸነፉን ጠቁሞ በውል ስምምነቱ መሰረት ከአያት አደባባይ ኮንዶሚኒየም፣ ከአቃቂ መንገድ አቃቂ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ከሲኤምሲ አደባባይ ካራሎ የሚወስዱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የዲዛይንና የቁጥጥር ስራ ያከናውናል፡፡

በተጨማሪም ከቦሌ አያት ሁለት እስከ ሰሚት ኮንዶሚኒየም የ43 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዲዛይን ጥናትና የግንባታ ቁጥጥር ስራ ለማካሄድ በ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ጨረታውን አሸንፎ የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡፡

በሌላ ቡኩል ቤዛ ኮሰልቲንግ ኢንጂነርስ የተባለ ሌላ አማካሪ ድርጅት ጆሞ አንድና ሁለት የኮንዶሚኒየም ቤቶች የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ፕሮጀክት ዲዛይንና የቁጥጥር ስራ ለማከናወን በ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ጨረታውን በማሸነፍ የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ድርጅቱ በአካባቢው በኮብል ስቶን የሚገነባውን የ18 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ዲዛይንና የግንባታ ቁጥጥር ስራ ለማከናወን የውል ስምምነት ፈርሟል፡፡

የገላን ሶስት ኮንዶሚኒየም የ17 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት ዲዛይን ጥናትና የቁጥጥር ስራ በ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ያሸነፈው ክላሲክ ኮንሰልቲግ ኢንጂነርስም የውል ስምምነት መፈረሙን ኢዜአ ዘግቧል።