አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21 2004 /ዋኢማ/ – በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ዳዋ ኦኮቴና ወርኢ በተባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የወርቅና የቤዝ ሜታልስ ክምችት መገኘቱን የብሄራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የብሄራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ በዛ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተገኘው የወርቅ ማዕድን ክምችት ሲመረት ለመንግሥት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ያስገኛል ።
በተለይም በኦሮሚያ ክልል በዳዋ ኦኮቴ የተገኘው ከ17 ሚሊዮን ወቄት በላይ የወርቅ ክምችት ኢትዮጵያን በዓለም የወርቅ ክምችታቸው ከታወቁት ቀዳሚ አገራት ተርታ ያሰልፋታል፡፡
በዚሁ አካባቢ ከተገኘው 550 ሺ ኪሎ ግራም ወርቅ 80 ሺ ኪሎ ግራም ያህሉን ለማምረት ዝግጅቱ መጠናቀቁንም አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡
በመጪዎቹ 20 ዓመታት ከሚገኘው የወርቅ ምርት ከግብር ገቢ ብቻ መንግሥት ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኝ ዋና ስራ አስፈጻሚዉ ገልጸዋል፡፡
በወርኢ ከሚመረተው ከ13 ሺ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ለመግንሥት ገቢ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
በአካባቢው ከተገኘው 18 ሺ ኪሎ ግራም ወርቅ በተጨማሪም የብር፣ የእርሳስ /ሊድ/ እንዲሁም የዚንክ ክምችቶች መገኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
የማዕድኖቹ ፍለጋና ምርመራ ስራ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ባለው የውጭ ድርጅት ተገምግሞ የሚያረካ ውጤት መገኘቱን ኢዜአ ዘግቧል።