የዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎች ችግር ፈቺ እንደሚሆኑ ተገለጸ

አድስ አበባ፤ ታህሳስ 23 2004 /ዋኢማ/ – የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራዎች አገሪቱ ካለችበት የልማት ጉዞ አኳያ የተቃኙና በሥራ ተተርጉመው የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ መሆናቸዉ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  አሥራ አንድ በሚሆኑ የተመረጡ ጉዳዮች የሚያደርገውን የተቀናጀ ምርምር በይፋ ለማስጀመር ያዘጋጀውን አውደጥናት አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንትና የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዲን ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው እያካሄዳቸው ያሉት ምርምሮች ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው፣ በተግባር የሚተረጐሙና ለኅብረተሰቡ የሚሰጧቸው ጥቅሞች የተለዩ ናቸው።

ከጥናቶቹ መካከል በትምህርት ጥራት፣ በምግብ ዋስትና፣ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተደረጉት ተጠቃሾች ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ዋና የምርምር ተቋም የመሆን ራእይ እንዳለው የገለጹት ፕሮፌሰር ማስረሻ፤ምርምሮችና ጥናቶች ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ እንዲደረጉ፣ ተመራማሪዎችንና ባለድርሻ አካላትን ያቀፉና የተቀናጁ እንዲሆኑ የሚያስችል ፖሊሲ አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ብዙ ችግር ፈቺ ሥራዎችን እንዲሠራ በሞጆ ቆዳ ፋብሪካ ፍሳሽ አጣርቶና ቆሻሻ አስወግዶ ንጹህ ውሃ የሚያወጣ የምርምር ውጤት ማስገኘቱን ጠቁመው፤ መምህራንና ተማሪዎች ወደተቀናጀ ምርምር እንዲገቡ በማበረታታት፣ አመች አሠራሮችን በመዘርጋትና ድጋፍ በማድረግ የቀድሞ አሠራሩን ፈትሾና ውጤታማነት ላይ አተኩሮ እየሠራ እንደሆነ አብራርተዋል።

የተቀናጀ ምርምር ማለት ለአንድ ዋና የምርምር ግብ ስኬት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የተለያዩ የምርምር ዘርፎች የተገናኙበትና የዩኒቨርሲቲውን ብቻ ሳይሆን የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ያካተተ እንደሆነም አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎች ዋና ኦፊሰር ዶክተር አስፋወሰን አሥራት በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲውን የታወቀ የምርምር ዩኒቨርሲቲ የመሆን ራዕይ ለማሳካት  ችግር ፈቺ እንደሚሆኑ ታምኖባቸው በተመረጡት አሥራ አንድ ዘርፎች ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉባቸው ምርምሮች እየተካሄዱ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ተግባራት ማስተማር፣ መማር፣ ምርምር ማድረግና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑ አገልግሎቶችን መስጠት በመሆኑ በአገሪቱና በኅብረተሰቡ ዉስጥ በሚኖሩ ችግሮች ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ሁሉ ቀጣይና ተከታታይ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ጥናት እያደረገባቸው ያሉት ችግሮች የትምህርት ጥራት፣ የምግብ ዋስትና፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የውሃ ሀብት፣ ብዝሃ ህይወት፣ የሰዎችና የእንስሳት በሽታዎች አማራጭ የኃይል ምንጭና ሌሎችም እንደሆኑ ተጠቁሟል።

ወደ 70 የሚደርሱ የምርምር ሃሳቦች ቀርበው አሥራ አንዱ በአገር ውስጥና በውጭ ተመራማሪዎች ተመርምረው እየተጠኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡ አውደጥናቱ በነገዉ ዕለት  በይፋ እንደሚጀመር እና በምርምር ሥራዎቹ የሚሳተፉና የሚተባበሩ የሚመለከታቸው አካላት እንደሚሳተፉ የዘገበዉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነዉ።