በሐረሪ ክልል የፀረ ወባ ዘመቻ ተካሄደ

ሐረር፤ ታህሳስ 24 2004 /ዋኢማ/ – በሐረሪ ክልል ከ55 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎችን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ የሚያስችል የፀረ ወባ መከላከያ መድሀኒት ርጭት ተካሄደ።

የክልሉ ጤና ቢሮ  የበሽታ መከላከል አስተባባሪ አቶ አብዱልሀሚድ አህመድ  እንደገለጹት በክልሉ የፀረ ወባ መድሀኒት ርጭት የተካሄደው ህብረተሰቡን  ሊከሰት ከሚችል የወባ ወረርሽኝ ሥጋት ለመጠበቅ ነው፡፡

በክልሉ በሚገኙ 130 ወባማ መንደሮች ባለፉት ሁለት ወራት በተካሄደው የጸረ ወባ መድሀኒት ርጭት 16 ሺህ 894 መኖሪያ ቤቶችን ለማዳረስ ተችሏል፡፡

በወባማ መንደሮች በተካሄደው የፀረ ወባ ርጭት ዘመቻ 694 ኪሎግራም የፀረ ወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉን የገለፁት አስተባባሪው ዘመቻዉ የአከባቢዉን
ነዋሪዎች ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ከበሽታው ስጋት ለመከላከል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ቢሮው ከመጪው ጥር ወር መግቢያ ጀምሮም ተጨማሪ የጸረ ወባ መድሀኒት ርጭት ዘመቻ ለማካሄድ ማቀዱንም አሰተባባሪው ገልፀዋል።