የተሻሻለው የሊዝ አዋጅ የከተማዋን የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 24 2004 /ዋኢማ/– አዲስ የተሻሻለው የሊዝ አዋጅ የከተማዋን የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

በባለሥልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የስራ ሂደት መሪ አቶ ሲሳይ ወርቅነህ እንደገለጹት ለመንገድ ግንባታ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የከተማዋ እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፋጠነ ነው፡፡

የመሬት ሥሪትና የአስተዳደሩ ዘመናዊ መሆን በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ይገጥም የነበረውን ችግር በማቃለል ግንባታን እንደሚያፋጥን ጠቁመዋል፡፡

በህጋዊም ሆነ በህገ ወጥ መንገድ በተያዙ ቦታዎች ምክንያት ፕላኑን የጠበቀ መንገድ ለመሥራት ብዙ ውጣ ውረድ ይገጥም ከነበረባቸው ምክንያቶች አንዱ በግንባታ ወቅት የሚነሳ የወሰን ማስከበር ጉዳይ ዋነኛው እንደነበር አመልክተዋል፡፡

በማንኛውም ሁኔታ የሚገኝ የመሬት ይዞታ በሕዝብና በመንግስት ቁጥጥር ሥር እስካለ ድረስ ችግሩ ፈጣን መፍትሄ እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል፡፡

ካለፉት 10  ዓመታት ወዲህ ከአጠቃላይ የከተማዋ ክልል 13 በመቶ በሚደርስ ቦታ ላይ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች ለመገንባት መቻሉን ጠቁመው ይህን ቁጥር በ20 12  ወደ 20  በመቶ ለማድረስ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም የሊዝ አዋጁ ፍትሐዊ የልማት ሥርጭት እንዲኖር ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው አቶ ሲሳይ አመልክተዋል፡፡

ለከተማዋ የመንገድ ግንባታ የጀርባ አጥንት የሆኑ ጥሬ ሃብቶችን ለማግኘት የመሬት ይዞታ በሕዝብና በመንግስት እጅ መሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቁመው ለገረጋንቲና ኮብል ስቶን ምርት አንድ ሚሊዮን 976  ሺ 666 ካሬ ሜትር ያህል ቦታ ለመያዝ መቻሉ የመሬት ስሪቱ ፖሊሲ ያስገኘው ውጤት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከመንገዶችም ባሻገር ለሌሎችም የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጠው ይህ የሊዝ አዋጅ ብዙሃኑን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ለመንገድ ሽፋኑ እድገት አዋጁ ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚኖረው ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡