አዲስ አበባ፤ታህሳስ 24 2004 /ዋኢማ/– የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባቱ ስራ ከዚህ በኋላ የአባይን ወንዝ አቅጣጫ የመቀየርና ውኃው ይሄድበት የነበረውን አካባቢ የመገንባት ተግባር እንደሚጀመር የግድቡ ፕሮጀክት ማናጀር ገለፁ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር ስመኘው በቀለ እንደገለፁት የግድቡ ስራ በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። በግድቡ የቁፋሮ ስራ እስካሁን ወደ 800 ሺ ሜትር ኪዩብ ያህል አፈርና ድንጋይ ከቦታው ማንሳት ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም ከቁፋሮው ስራና የወንዙን አቅጣጫ ለማስቀየር እየተከናወኑ ካሉት ተግባራት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ዘመናዊ ማሽነሪዎች በቦታው ደርሰዋል።
ኢንጂነር ስመኘው እንዳሉት ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው በስፍራው የደረሱት ማሽነሪዎች አጠቃላይ ስራውን በማቀላጠፍ ረገድ ከፍተኛ ልዩነትን መፍጠር ችለዋል።
ለግንባታ ስራው አስፈላጊ የሆኑ ምቹ ሁኔታዎች በሚፈለገው ደረጃ ተፈጥረዋል ያሉት ኢንጂነር ስመኘው መንገዶችም ስራውን ለማከናወን በሚያስችል ደረጃ መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።
እንደ ኢንጂነር ስመኘው ገለፃ በአሁኑ ወቅት ግድቡ በሚገነባበት ቦታ 1ሺ 500 ያህል የሃገር ውስጥና 85 ያህል የውጭ ሃገር ዜጎች ሌት ተቀን እየሰሩ ናቸው። ለሠራተኞች መኖሪያና ለሌሎች አገልገሎቶች የሚያስፈልጉ ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። ስራው ተለወዋጭ እንደመሆኑ መጠን የቤቶቹ ግንባታም ሆነ የሰው ኃይሉ እንደአስፈላጊነቱ በየጊዜው እንደሚጨምር ኢንጂነር ስመኘው ጠቁመዋል።
ለግድቡ ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎች ግዥ በሃገር ውስጥና በውጪ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ኢንጂነር ስመኘው ከእነዚህ መሳሪያዎች ውስጥም የተወሰኑት ከግንባታው ሥፍራ ደርሰዋል፤ የግድቡን የተለያዩ ክፍሎች ለመገንባት በሚያስችል ሁኔታም መሳሪያዎች በመተከል ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኢንጂነር ስመኘው እንዳሉት ለግድቡ ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎችን በማቅረብ ረገድ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ድርሻ ላቅ ያለ ነው።
ዋናው ግድብ የሚያርፈበት የከርሰ ምድር ጥናት 70 በመቶ ያህል ተጠናቋል ያሉት የፕሮጀክት ማናጀሩ እስከ 130 ሜትር ጥልቀት በመውረድ እስካሁን በተሰራው የፍተሻ ስራ ምንም ዓይነት የከርሰ ምድር ችግር አለመከሰቱን ገልፀዋል።
በስራው ሂደት አስቸጋሪ የሚባሉት ሁኔታዎች ቀድመው ያለፉ በመሆናቸው አሁን ሁሉም ነገር በታሰበው ደረጃ ያለምንም ችግር እየተከናወነ እንደሚገኝ የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው ።