በመንገድ ልማት በአምስት ዓመቱ በእቅድ ከተያዘው ውስጥ 23 በመቶ ተከናወነ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26 2004 /ዋኢማ/ – በመንገድ ዘርፍ ልማት በአምስት ዓመቱ በፌዴራል ደረጃ በእቅድ ከተያዘው ውስጥ እስካሁን 23 በመቶ መከናወኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ  እንደገለፁት ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም  የታቀደው የመንገድ ዘርፍ መርሃ ግብር መጠነ ሰፊና በርካታ መገለጫዎች ያሉት ነው።በአምስት ዓመቱ በፌዴራል ደረጃ  ሊሰራ በእቅድ ከተያዘው ውስጥ እስካሁን 23 በመቶ ያህል መከናወኑንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ ሳምሶን ማብራሪያ በአምስት ዓመት ውስጥ ለፌዴራል መንገድ ብቻ ከ81 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል። ወደ 99 ሺ 431 ኪሎ ሜትር መንገድም ይሰራል። ይህ ደግሞ ባለፉት 14 ዓመታት ከተሰሩትም የሚበልጥ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በአምስት ዓመት ውስጥ  ወቅታዊና መደበኛ ጥገናን ጨምሮ የዋናና አገናኝ መንገዶችን ደረጃ የማሻሻልና የማጠናከር እንዲሁም የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ እንደሚካሄድ አቶ ሳምሶን ጠቁመዋል።
በፌዴራል ደረጃ  ከሚሰሩት በተጨማሪ በአምስት ዓመቱ እቅድ ወረዳን ከዋና መንገድ ጋር ለሚያገናኙ መንገዶችም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል።

በመላው ሃገሪቱ ካሉት ቀበሌዎች ውስጥ 39 በመቶ ያህሉ ብቻ  ከዋና መንገድ ጋር የተገናኙ ሲሆን እስከ 2007 ዓ.ም መጨረሻ ሁሉንም ቀበሌዎች ከዋና መንገድ ጋር ለማገናኘት  የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም ተቀርጿል።ፕሮግራሙን ተግባር ላይ ለማዋል እስካሁን  የዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል ያሉት  አቶ ሳምሶን  አሁን ወደ ተግባር በመሸጋገር ላይ በመሆኑ ለበርካታ አገር በቀል የስራ ተቋራጮች የስራ እድል እነደሚፈጥር ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ  በአሁኑ ወቅት በርካታ የስራ ተቋራጮች ተደራጅተው ወደ ግንባታ ለመግባት የሚያስችላቸውን የኮንትራት ውል በመፈራረም ላይ ናቸው። ወደ ግንባታ ስራ የተሸጋገሩ የስራ ተቋራጮችም አሉ።

የመንገድ ስራውን ለማስፈጸም የተለያዩ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ያስፈልጋሉ ያሉት አቶ ሳምሶን መሳሪያዎቹ በሃገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የስራ ተቋራጮቹ የአቅም ውስንነት ያለባቸው እንደመሆኑ መሳሪያዎቹ ወደ የክልሎቹ ከተሰራጩ በኋላ በረጅም ጊዜ መሳሪያዎቹን እንዲያገኙ እንደሚደረግ ዳይሬክተሩን ጠቅሶ የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።