በደቡብ ክልል 215 የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 26 2004 /ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል ባለፈው የበጀት ዓመት የተገነቡ 215 የጤና ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ ።

ቢሮው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው  ሰሞኑን ለአገልግሎት የበቁት የጤና ጣቢያዎች የተገነቡት ቀደም ሲል መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች ባልተስፋፉባቸው የገጠር ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ  ነው::

በቢሮው የሕዝብ ግንኙነትና የመንግሥት ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ቀድረላ አህመድ እንደገለፁት የጤና ጣቢያዎቹ አሥፈላጊው የውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች እና የሰው ኃይል ተሟልተውላቸው ለሕብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

ለአገልግሎት የበቁት የጤና ተቋማት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች እና ተጎራባች ሕዝቦች አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳላቸው አቶ ቀድረላ ተናግረዋል።

የጤና ጣቢያዎቹ ግንባታ የተካሄደው በክልል እና በፌደራል መንግሥት ድጋፍ ሲሆን በአጠቃላይ ከ 852 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋል።

ቢሮው በቀጣይ የጤና አገልግሎት ሽፋንን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማዳረስ የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የሥራ ሂደት ባለቤቱ በተያዘው በጀት ዓመትም የ 82 አዳዲስ የጤና ጣቢያዎች ግንባታ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ግንባታቸው የተጀመሩት የጤና ጣቢያዎች ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በኋላ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ አሁን 97 በመቶ ላይ ያለውን የክልሉን የጤና አገልግሎት ሽፋን መቶ ከመቶ እንደሚያደርሱ አቶ ቀድረላ  አመልክተዋል።

በደቡብ ክልል በአሁኑ ወቅት 3 ሺህ 602 ጤና ኬላዎች፣ 672 ጤና ጣቢያዎች፣ 17 ዞናል ሆስፒታሎችና ሦስት ሪፈራል ሆስፒታሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።