አዲስ አበባ፤ታህሳስ 27/2004/ዋኢማ/- በአዲሱ የከተማ መሬት የሊዝ አዋጅ ላይ የአስፈፃሚ አካላተ በቂ ግንዛቤ ይዘው ለህብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ መስጠት እንዳለባቸው ተገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የተሳተፉ የፍትህ ሴክተር ሰራተኞች ስለአዋጁ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ትናንት በኢትዮጵያ ካርታ ሥራዎች ድርጅት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከ116 ወረዳዎች ለተውጣጡ 1 ሺ 300 የፍትህ ሴክተር ሰራተኞች በአዲሱ የሊዝ አዋጅ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ኃይለማርያም አዋጁ መንግስት የመሰረተ ልማቶችን እንዲያስፋፋ ከማገዙም በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ልማትን በማፋጠን የከተማውን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል አብራርተዋል።
የአስፈፃሚ አካላትም የአዋጁን ጠቀሜታ ተረድተው መላውን ህብረተሰብ ማሳወቅ አለባቸው ያሉት ኃላፊው የአዋጁ ተፈፃሚነት ሰራተኛውን ጨምሮ ብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል እና ልማታዊውን ባለሀብት እንደሚጠቅምም ተናግረዋል።
አንዳንድ የመድረኩ ተሳታፊዎችም በተለይ በየወረዳው አዋጁን በሚመለከት የሚታዩ ችግሮችን አንስተዋል።
የወረዳ አመራሮችና የባለድርሻ አካላት ስለ አዋጁ በቂ ግንዛቤ ማጣት፣ ከህብረተሰቡ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች አመራሮች በቂ ምላሽ አለመስጠት፣ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን አለማመቻቸት በተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው።
ከዚህ ቀደም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአዋጁ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ሆኖም ግን በአግባቡ ወደ ህብረተሰቡ አለመድረሱን የመድረክ መሪዎች አብራርተዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩም በየደረጃው የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ታስቦ መዘጋጀቱንና ተመሳሳይ መድረኮች በሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከታህሳስ 25 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።
አንዳንድ የውይይቱ ተካፋዮችም ከመድረኩ ጥሩ ግንዛቤ ማገኘታቸውን ገልፀዋል።
ከኮልፌ ቀራኒዮና ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በውይይቱ ላይ የተገኙት አቶ አንሙት ፋየ እና አቶ አሰግድ ታፈሰ ቀድሞ ስለ አዲሱ አዋጅ የተሳሳተ መረጃ እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ከውይይት መድረኩ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና በቀጣይ ለህብረተሰቡ ትክክለኛውን መረጃ እንደሚያደርሱም ጠቁመዋል።
አዲሱ የከተማ መሬት የሊዝ አዋጅ ከህዳር 18 ቀን 2004 ጀምሮ በነጋሪት ጋዜጣ ፀድቆ በሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል።