በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና አሸባሪዎችን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን የሚከላከል አሰራር ሊተበገር ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 30 2004 /ዋኢማ/ – በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና አሸባሪዎችን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችል አሰራር ሊጀምር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡

ወንጀሉን ለመከላከል ሁሉም ባንኮች ከመጪው ጥር 1 ቀን 2004 ጀምሮ ከተወሰነ መጠን በላይ የሚደረግ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለፋይናንስ መረጃ ደህንነት ማዕከል የሚያሳውቁበት አሰራር ይጀምራል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ዋና ገዢ አቶ ጌታሁን ናና ሰሞኑን ከባንኮች ኃላፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት እንዳሉት በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና አሸባሪዎችን በገንዘብ መደገፍ ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡

ከወንጀል ድርጊቶቹ መካከል አደንዛዥ ዕጽ ማዘዋወር፣ የታክስ ስወራና ሰው ማዘዋወር እንደሚጠቀሱም አመልክተዋል፡፡

ድርጊቱ ከወንጀልነቱ ባሻገር የፋይናንስ አለመረጋጋት በመፍጠር በአገሪቱ እድገትና ገጽታ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚያሳድርም አመልክተዋል፡፡

ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያስችልም መንግሥት የፋይናንስ መረጃ ደህንነት ማዕከል በዓዋጅ ማቋቋሙን አቶ ጌታሁን አስታውቀዋል፡፡

የፋይናንስ መረጃ ደህንነት ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር እንዳሉት ማዕከሉ በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና አሸባሪዎችን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተብሎ ተቋቁሟል፡፡

ማዕከሉ በሁሉም ባንኮች በግለሰብና በድርጅት የሚደረግ ማንኛውንም ከ200 ሺህ ብር በላይ፣ ከ10 ሺህ በላይ ዶላር ወይንም ከዚህ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ሪፖርት መሰብሰብ እንደሚጀምርም ገልጸዋል፡፡

ጥርጣሬ ያለበት ዝውውር ሲያጋጥም የገንዘብ መጠኑ አስፈላጊ አለመሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ ፈትለወርቅ፣ ማዕከሉ ሥራውን ለመጀመር አስፈላጊውን የሰው ኃይልና ቁሳቁስ እያሟላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከተጠቀሰው መጠን በላይ የሆነ የገንዘብ ዝውውር የሚያደርግ ግለሰብም ሆነ ድርጅት በወንጀል ተጠርጥሯል ማለት እንዳልሆነም አብራርተዋል፡፡

የወንጀል ድርጊቱ ከውጪ ወደ አገር ውስጥና ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ ጭምር ስለሚካሄድ ሁሉም ባንኮች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸው ኃላፊዋ አሳስበዋል፡፡

በባንኮች የተጀመረው ወንጀሉን የመከላከል ሥራ በሌሎች የፋይናንስና የፋይናንስ ባልሆኑ ተቋማት ጭምር እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ የደንበኞችን ምስጢር ከመጠበቅ አኳያ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

ከባንኮች በደረሰው ሪፖርት ላይ ወንጀሉ እንደተፈጸመ ሲያምን ማዕከሉ ጉዳዩን ወደሚመለከተው የፍትህ አካል በማቅረብ ክስ እንዲመሰረት እንደሚያደርግ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ የወንጀል ድርጊቱን አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚካሄድና ጉዳዩ የኅብረተሰቡን ከፍተኛ ትብብር እንደሚሻ ማሳሰባቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡