ሀዋሳ፤ ታህሳስ 30 2004 /ዋኢማ/ – የደቡበ ክልል የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ለተለያዩ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች 551 ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተሮችን ማከፋፈሉን አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አይናለም ጸጋዬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት ሰሞኑን የተከፋፈሉት የላፕ ቶፕ ኮምፒዩተሮች ከ 5 ሚሊዮን 569 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ናቸው፡፡
የላፕ ቶፕ ኮምፒዮተሮቹ የተከፋፈሉት በክልሉ በሚገኙ 14 ዞኖች ውስጥ ለ134 ወረዳዎችና ለ21 የከተማ አስተዳደሮች ነው፡፡
የላፕ ቶፕ ኮምፒዮተሮቹ በክልሉ ባለፈው የበጀት ዓመት በተካሄደው አስተዳደራዊ መዋቅር ጥናት ውጤት መሠረት በመረጃ አያያዝ ችግር ሠፊ ክፍተት ያለባቸው ተቋማትን በመለየት የተከናወነ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
ኮምፒዮተሮቹ የየዘርፉ ባለሙያዎች የተቀላጠፈ የሥራ አፈጻጸም እነዲኖራቸው እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው የላፕ ቶፕ ኮምፒዮተሮቹን ከማሠራጨት በተጨማሪ ለ368 ባለሙያዎች መሠረታዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥልጠናዎችን መስጠቱን ከዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡