አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30 2004 /ዋኢማ/ – የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ግልፅነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን መጀመሩን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር አስታወቁ።
ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ኮሚቴው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ጥናትን በመገምገም በሀገራቱ መካከል ይበልጥ ግልጽነትን ለመፍጠር የተቋቋመ ነው።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሱዳን እና በግብፅ ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ የለውም ያሉት ሚኒስትሩ ሆኖም ሁለቱ ሀገራት ያደርስብናል ብለው ለሚገምቱት ችግር ግልፅነት ለመፍጠር የተጠናውን ጥናት እንዲገመግም በተደረሰው ስምምነት መሰረት ኮሚቴው መቋቋሙን ተናግረዋል።
ኮሚቴው ከየሀገራቱ ሁለት ሁለት ባለሙያዎችን በማካተት የተቋቋመ ሲሆን፤ በተጨማሪም አራት በውኃው ዘርፍ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እንደሚካተቱበትም ገልፀዋል።
ኮሚቴው የመጀመሪያውን ስብሰባ በአዲስ አበባ ያካሄደ ሲሆን፤ ሁለተኛውን ስብሰባም በሱዳን ለማካሄድ መቀዱን አስረድተዋል።
በመጀመሪያው ስብሰባም ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን በምን አይነት መልኩ ማካተት እንደሚቻል መስፈርት የማውጣት ስራ መካሄዱንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
የህዳሴው ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያመጣ ኢትዮጵያ እንደምታምን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ የግብፅና የሱዳን የውኃ ሚኒስትሮች የግድቡ ስራ ቆሞ የጥናቱ ግምገማ እንዲጠናቀቅ ፍላጎት ቢያሳዩም ኢትዮጵያ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያመጣ በማመኗ ስራውን በማካሄድ ላይ መሆኗን ተናግረዋል።
ኮሚቴው እንዲቋቋም የተወሰነው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ ባካሄዱት ስብሰባ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።