አዲስ አበባ፤ ጥር 01 2004 /ዋኢማ /-በአርባ ምንጭና በአካባቢው የሚመረተውን የተፈጥሮ ሙዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዉጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን የኢትዮጵያ ሆርቲ ካልቸር ኤጀንሲ አስታወቀ ።
ጥራቱን በጠበቀ ዘመናዊ መንገድ ምርቱን ሰሞኑን ለዉጭ ገበያ ማቅረብ የተጀመረዉ ከአውሮፓና መካከለኛ ምስራቅ ሀገር ኩባንያዎች ጋር በተደረገው ድርድር በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የተሻለ ገበያ በመገኘቱ ነው።
በኤጀንሲዉ የተፈጥሮ ሙዝ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ገረመው ቀና እንደገለፁት አትስ ራጋዳን ከተባለ የሳውዲ ዓረቢያ ኩባንያ ጋር በተደረሰዉ ስምምነት መሰረት በየሳምንቱ 200 ቶን የተፈጥሮ ሙዝ ለዉጭ ገበያ ይቀርባል ።
ከአርባ ምንጭና አካባቢው የሚሰበሰበዉን ሙዝ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በፕላስቲኮችና በካርቶን በማሸግና የተለያዩ የማጓጓዣ ዘዴዎችን በመጠቀም ካለፈዉ ቅዳሜ ጀምሮ መላክ መጀመሩን አስተባባሪው አስታዉቀዋል ።
እንደ አቶ ገረመው ማብራሪያ ምርቱ በዓለም ገበያ ያለዉን ተፈላጊነትና ተወዳዳሪነት እንዲሁም የጥራት ደረጃዉን ለማሳደግ ከደቡብ ክልል ግብይትና ህብረት ስራ ዩኒየንና ከጋሞ ጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ጋር በመሆን ኤጀንሲዉ እየሰራ ይገኛል።
በዚህም እንቅሰቃሴ የአርሶ አደሮቹ የምርት አሰባሰብና አያያዝ፣ ክህሎትና ግንዛቤ በማሳደግ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግም ኤጀንሲዉ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
በጋሞ ጎፋ ዞን ሙዝ አብቃይ ወረዳዎች በ7 ሺህ 912 ሄክታር መሬት በተሸፈነው የተፈጥሮ ሙዝ ምርት በዓመት በአማካይ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ጥራቱን የጠበቀ ምርት የመሰብሰብ አቅም እንዳለም ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃም አመልክቷል።
በዞኑ በዋናነት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ፣በምዕራብ ዓባያ፣ በዳራማሎ፣ በኡባ ደብረ ፀሃይና አይዳ ወረዳዎች ከ10 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሙዝ ማምረት ስራ ላይ መሰማራታቸዉንና ከእነዚህ መካከል 1ሺህ 500 የሚሆኑ በጋሞ ጎፋ አትክልትና ፍራፍሬ ዩኒየን ስር በተደራጁ 18 መሰረታዊ ማህበራት የታቀፉ መሆናቸዉን የዘገበው ኢዜአ ነው ።