በደቡብ ክልል የሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ እያደገ ነው

ሀዋሳ፤ ጥር 16 2004 /ዋኢማ/- በደቡብ ክልል በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው ቀደም ሲል በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው የሴት ተማሪዎች ጥቅል የትምህርት ተሳትፎ በአሁኑ ወቅት 96 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷል።

በተለይ በ2001 የትምህርት ዘመን 89 ሺህ 998 የነበረው የሁለተኛ ደረጃ የሴት ተማሪዎች ቁጥር በ2004 የትምህርት ዘመን 125 ሺህ 913 መድረሱን በቢሮው የሥረዓተ ፆታ የሥራ ሂደት አስተባባሪ  ወይዘሮ አስቴር ሐንቃሞ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት አንድ ሚሊዮን 765 ሺህ ታዳጊ ሴቶች በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመግባት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙም የሥራ ሂደት አስተባባሪዋ አስረድተዋል።

የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ሊጨምር የቻለው ከወላጆች፣ ከመምህራንና ከወረዳ የሴቶችና የወጣቶች ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመቀናጀት በሴቶች ላይ የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመከናወናቸው መሆኑን  አስረድተዋል።

እንዲሁም ሴቶች በቤት ውስጥ ያለባቸውን የሥራ ጫና ከግምት ያስገባ የማካካሻ የትምህርት ክፍለ ጊዜ መዘጋጀቱ፣ ለችግረኛ ሴት ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች መቅረባቸው እንዲሁም  የተለያዩ  የድጋፍ ሥራዎች መከናወናቸው ተሳትፎአቸውን እንዳሳደገው ተናግረዋል።

እንደ አስተባባሪዋ ማብራሪያ ቢሮው በተያዘው የትምህርት ዘመንም  የሴት ተማሪዎች ማቋረጥን እና በክፍል የመድገም መጠንን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ለዚህም በክልሉ በሚገኙ ሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሴት ተማሪዎች ከወላጆች እና ከመምህራን ከሚደረጉ እገዛዎች በተጨማሪ የተሻለ የትምህርት አፈጻጻም ያላቸው ሴት ተማሪዎች ዝቅተኛ አፈጻጻም ካላቸው ጋር እርስ በእርስ በመደጋገፍ ዉጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ አደረጃጀቶች መዘርጋታቸውን ጠቁመዋል።

የትምህርት ጥራት ፓኬጁን በተሟላ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ የሴት ተማሪዎችን ውጤታማነት ማሻሻል ይጠይቃል ያሉት አስተባባሪዋ የባለድርሻ አካላት ለሴቶች ትምህርት ተሳትፎ ማደግ የበኩላቸውን ሚና ማበርከት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።