የሊባኖስ መንግስት በቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ላይ በደረሰው አደጋ ያወጣው ሪፖርት መሠረተ ቢስ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ጥር 09 2004 /ዋኢማ/ – የሊባኖስ የትራንስፖርት እና የሕዝብ አገልግሎት ሚኒስቴር በበረራ ቁጥር ኢት-409 ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ላይ ለደረሰው አደጋ ፓይሌቱን ተጠያቂ በማድረግ ያወጣው ሪፖርት መሠረተ ቢስ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት የደረሰው አደጋ የመጨረሻ ሪፖርት በሊባኖስ መንግስት በትናንትናው ዕለት ይፋ ተደርጓል። ሪፖርቱም በአውሮፕላኑ ላይ ለደረሰው አደጋ ፓይሌቱንና ረዳቱን ተጠያቂ አድርጓል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የሊባኖስ መንግስት ከአደጋው ማግስት ጀምሮ የዓለም አቀፉን የሲቪል አይቬሽን ድርጅት ሕግ በሚቃረን መልኩ ፓይሌቱንና ረዳቱን ተጠያቂ  አድርጓል። የመጨረሻው ሪፖርትም ያንንኑ ማስተጋባቱ አላስደነቀንም ብለዋል አቶ ተወልደ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የሲቪል አይቬሽን ባለሥልጣን ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ የምርመራ ሂደቱም ሆነ የመጨረሻው ሪፖርት በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌላቸው አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሪፖርቱ ሚዛናዊነት የጎደለው፣ትክክልኛ መረጃ የሌለው፣ ያልተሟላ እና የአደጋውን አጠቃላይ ይዘት የማያንፀባርቅ ነው።

የሊባኖሰ መንግስት የተጓዦችን ማንነት፣ የአውሮፕላኑን 92 ከመቶ ስብርባሪ እና ሌሎች ጠቃሚ ሪፖርቶችን ለኢትዮጵያ ለመስጠት እስካሁን ፍቃደኛ እንዳልሆነ ያስረዱት አቶ ተወልደ የአደጋው ሰለባ የሆኑ ሰዎች አስክሬን ሳይመረመር መቀበሩንና የመንገደኞችን ሙሉ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑንም አብራርተዋል።

አውሮፕላኑ የወደቀው በፓይሌቱና ረዳቱ ችግር ሳይሆን ከውጭ በደረሰበት ጉዳት ሊሆን አንደሚችል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ኦፕሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ ካፒቴን ደስታ ዘሩ በበኩላቸው የአይን እማኞችና በጊዜው በአከባቢው ላይ ሲሰሩ የነበሩ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አደጋው ከመከሰቱ በፊት በአውሮፕላኑ አቅጣጫ የሚሄድ እሳት አንዳዩ አየር መንገዱ መረጃ ማግኘቱን ጠቁመዋል።

ሁሉም የዲጂታል የበረራ መረጃ መቅጃዎች አውሮፕላኑ በ1 ሺ 300 ጫማ ከፍታ ላይ እንዳለ መቆማቸውን የተናገሩት ካፒቴን ደስታ ከአብራሪዎች ክፍል በተገኘውና ለመጨረሻ ጊዜ በተቀረፀው ድምፅም ትልቅ ፍንዳታ ተሰምቷል ብለዋል።

እነዚህ ሁሉ ሰነዶች የሚያሳዩት አወሮፕላኑ የወደቀው በመሳሪያ ተመትቶ፣ በመብረቅ አሊያም አሻጥር ተሰርቶበት ሊሆን አንደሚችልም ገልጸዋል።

ሁለቱም አብራሪዎች በአግባቡ የሰለጠኑና ብቁ ባለሞያዎች መሁናቸውን ያስታወቀው የአየር መንገዱ፤ ዋና አብራሪውም የሃያ አመት ልምድና ከ10 ሺ ሰአት በላይ በረራ ያከናወነ ነው ብሏል።የአውሮፕላኑ ሰራተኞችም የሙያ ልምዳቸው በሰርተፊኬት የተረጋገጠ እንደሆነ አብራርተዋል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የሊባኖስ መንግስት የአደጋውን መንስኤ የካፒቴኑ ስህተት አድርጎ ሪፖርት ማውጣቱ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አየር መንገዱ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአራት አህጉራት 63 መዳረሻዎች ሲኖሩት በቅርቡ የምርጥ አየር መንገዶች ስብስብ የሆነው ስታር አሊያንስ አባል መሆ